ህሊና – የስሜት፣ የማመዛዘን፣ የግንዛቤና የድርጊት ድምር ውጤት

የኪነጥበብ ባለሙያው ጸሐዬ ዮሐንስ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተምሳሌት ለሆነችው ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ “ህሊና” በሚል ርእስ ባቀነቀነው ዜማ ግጥሞች ውስጥ ስለ ህሊና ግዝፈት ሰጥቶ እንዲህ ይላል ፡፡
ህሊና … ህሊና … እንደ እርሷ ሁሉም ቢሆን ቀና
የሚያየው ትልቁን ነውና – ቅንነት በጎነት ነውና
ከበጎ በስተቀር ክፋት – አትመልከች ብሎ ፈጥሯት
መንገዷን እራሷ ታውቃለች – አትወድቅም ሰው ትደግፋለች
ጽናት ላወረሳት ልዕልት – ድል አብሳሪ ኮከብ ንግስት
በጠራራ ጸሃይ ቢያጧት – እስከ አሁን የትነበርሽ ያሏት…እያለ ይቀጥላል::
ዶክተር ጠና ደዎ “ሰው፣ግብረገብና ስነምግባር” የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንዳሰፈሩት – ህሊና በራስ ውስጥ የሚገኝንም ሆነ በውጭ ያሉ ነገሮች የማዋሃድና የመገንዘብ ጥራት ነው፡፡
ህሊና ስለ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ነገሮች ያለውን ሁኔታ ወይም እውነታ በመረዳት፣ እውቀትን በማሳደግና በመልካም እሴቶች ላይ በመመስረት ትውልድን ተጠቃሚ የሚያደርግና እሴትን የሚጨምር ተግባር በማከናወን አሻራን ማኖር የሚያስችል የስብዕና መገለጫ መሳሪያ ነው፡፡
ንጹሕ ህሊና ያለው ሰው – ክፋት ስለማያስብበት አእምሮው የጸዳ ነው፡፡ መጥፎ ተግባር ስለማይፈጽምበት – እጁም የጸዳ ነው ፡፡ ጸያፍ ቃል ስለማይናገርበት – ምላሱም የጸዳ ነው፡፡ የማይገባ ቦታ ስለማይረግጥበት – እግሩም የጸዳ ነው ፡፡ ለዚህም ነው ከመልካም እሴቶች ቀዳሚ የሆነው ህሊና እጅግ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ፡፡
ኅሊና ስሜትን ትቶ ግንዛቤን ብቻ በደረቁ የሚቀበል አይደለም፤፡ ህሊና የስሜት፣ የማመዛዘን ፣የግንዛቤና የድርጊት ውህደት ውጤት መሆኑን ምሁራን ያሰምሩበታል፡፡
ህሊና ሀዘንንና ደስታን ወይም ጥቅምንና ጉዳትን በጭፍኑ የሚያስተናግድ ሳይሆን የሚያሳዝንንና የሚያስደስትን፣ የሚጠቅመንንና የሚጎዳንን እንዲሁም መልካሙንና ክፉውን ለይቶ ሁሉንም ክስተቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድናስተናግድ የሚያስችለን ሰብዓዊ እሴት ነው፡፡
ህሊና ሰዎች መልካም እሴቶችን እንዲመረምሩ ፣ እንዲረዱና ከዚህም አኳያ ያለቸውን መብትና ግዴታ በአግባቡ እንዲወጡ፣ የራሳቸውን ምርጫዎች እንዲወስኑና ማስተካከል እንዲችሉ የድርጊቶችን ግብረገባዊና ኢ- ግብረገባዊ ይዘቶች እንዲገመግሙ የሚያስችል ሲሆን ህሊና የውስጣዊና ውጫዊ የህይወት መርህሆዎች ውህደት ውጤትና የተግባራት መመዘኛ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡
በአጭሩ ህሊና ማለት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለ ግብረገባዊ የአእምሮ ብይን ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው የድርጊት መመሪያ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ሲሆን ለሁሉም የሰው ልጆች እንቅስቃሴዎች ህግ ማውጣትም የማይሞከር ነው፡፡
ሰዎችን ልዩ ከሚያደርጓቸው ባህርያት መካከል ከህግ ይልቅ በህሊና ዳኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የመምራት አቅም ያላቸው ብቸኛ ፍጡራን መሆናቸው ነው፤
ይህ ትክክል ነው – መሆን ወይም ማድረግ አለብኝ፡፡
ያ ትክክል አይደለም – መሆን ወይም ማድረግ የለብኝም ብሎ የመዳኘት ችሎታ ያለው ፍጡር የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጆች ህሊና – ስህተት ካለ ልክ አይደለም – ድርጊቱ መኮነን ወይም መወገዝ አለበት የሚል ሲሆን አድራጊውንም መወገዝ ወይም መቀጣት አለበት ይላል ፡፡
ህሊና በተሰራው በጎ ነገር እንድንደሰት – በተፈጸመው ሰህተት እንድንጸጸት ያደርገናል፡፡ በተጨማሪም ውስጣዊ ህይወታችንን ከሚጎዱ ነገሮች በመከላከል ስጋትና ጭንቀትን ፣ ፍርሃትና ጥርጣሬን አስወግዶ በራሳችን ውስጥ የነጻነት ስሜትና በራስ የመተማመን አቅማችንን እንድናጎለብት ይረዳናል፡፡
አንድ ግለሰብ ለህሊና ፍርድ የሚያበቃውን ግብረገባዊ እሴቶች፣ ህግጋትን፣ ብይንንና የተለያዩ የህይወትና የአኗኗር መርሆዎችንን የሚያገኘው ከሚኖርበት የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ህሊና በግለሰብ ውስጥ ያለ የህብረተሰብ ድምጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ህብረተሰብ በእያንዳንዱ ሰው ህሊና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ያህል የእያንዳንዱ ግለሰብ ህሊና አቀራረጽም በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ስለዚህ አንድ ግለሰብ ለህብረተሰቡ ግብረገባዊ ህይወት መበልጸግ የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይደለም ማለት ነው ፡፡
የሰው ልጆች ህሊናዊ ባህርይና ጠባይ በከፊል በግል እንቅስቃሴ በከፊል ደግሞ በአካባቢው ማህበረሰብ ተጽዕኖ ይቀረጻል፡፡
በእርግጥ አካባቢ ለሰው ልጅ የህሊና እድገት ውጫዊ ሁኔታ ነው፡፡ይሁን እንጂ የሰውን ውስጣዊና ውጫዊ ህሊና ከመቅረጽ አንጻር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡
የሰው ልጆች ህሊና የሚቀረጸው በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ የህብረተሰብ እሴቶች የተገነባ ሲሆን ለምሳሌ የተፈጥሮ አካባቢ ማለትም የአየር ሁኔታ ፣ የአፈር ለምነት ፣ የተለያዩ ማእድናት መኖርና ወይም አለመኖር በሰው ባህርይ አቀራረጽ ላይ የራሳቸው አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ በእነዚህ የተፈትሮ ውጤቶች አጠቃቀማችን አንጻር እንኳን – አካባቢ የሚያተጋ ወይም የሚያሰንፍ ሊሆን እንደሚችል ልናስተውል ይገባል፡፡
ለሰው ልጆች ህሊና እድገት ጉልህ ድርሻ ካላቸውና የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት መካከል ወላጆች፣ የቤተሰብ አባላት ፣የሃይማኖት አባቶች ፣ መምህራን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ጓደኞች፣ ት/ቤቶች፣ የሃማኖት ተቋማት ፣መገናኛ ብዙሃን ፣ሲቪክ ማህበራት ፣ መጻሕፍት ፣ቲያትርና ፊልም፣ የተሰማራንበት የስራ መስክና የስራ ቦታዎችና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በእርግጥ የሰው ልጅ በአካባቢው ውስጥ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ባያስተውልም ከባህርይውና ከፍላጎቱ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ወይም ሊስማሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ወይም ነገሮችን ለይቶና መርጦ ያስተውላቸዋል – ያስባቸዋል – ይገነዘባቸዋል፡፡
ከባህርይው ጋር የማይሄዱና ቀጥተኛ ተዛምዶ የሌላቸውን አካባቢያዊ ነገሮች ሊተው ወይም ትኩረት ላይሰጣቸው ይችላል፡፡ሰው በአካባቢው ይለውጣል – እርሱም አካባቢውን በመለወጥ የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡
በዚህ መሰረት በህሊና ላይ የተመሰረተ ግለሰብ ተግባር ለእራሱ፣ ለቤተሰብ ፣ ለማህበረሰብ ፣ለሃገርና እልፍ ሲልም ለአለም የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በውል በመገንዘብ አገልጋይነት፣ ትጋትና ስኬትን ሰንቀን ለገራችን ልማትና እድገት የተሻለ ብርሃን መፈንጠቅ የሚያስችሉ ተግባርና ሃላፊነቶቻችንን በብቃት በመወጣት የሃገራችንን ራዕይ ለማሳካት ሁላችንም በጋራ እንድንረባረብና በቅንጅት እንድንሰራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል፡፡
ምንጭ ፡- ዶክተር ጠና ደዎ “ሰው ፣ግብረገብና ስነምግባር” የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *