ተፈፃሚነቱ አሁንም የሁላችንንም ቁርጠኝነት ይፈልጋል

                                          የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000
አካል ጉዳት በማንኛውም ሰዓትና ሁኔታ ከውልደት እስከ ህልፈት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በተፈጥሮ እና በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት እክሎች ያሉባቸው ሰዎች እኩል እድል ይበልጥ ይረጋገጥ ዘንድ በብሔራዊ፣ በአህጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን ሀገራችን ተቀብላ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ እነኝህን የህግ ማእቀፎች ተከትሎ መስራትና የህግ ማዕቀፎቹ ወደመሬት ወርደው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ሀገራት በገቡት ስምምነት መሰረት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በፖለቲካዊና ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የህግ ማእቀፎችን በማውጣት እንዲሁም የማህበራዊ ጥበቃ ማዕቀፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡
በዓለም ጤና ድርጅትና በአለም ባንክ የዳሰሳ ጥናት መሰረት በሀገራችን ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ይገመታል፡፡ ይህን ቁጥር ከግምት ባስገባ መልኩ አካል ጉዳተኞች በሁሉም አይነት ሰብዓዊ መብቶችና መሰረታዊ ነፃነቶች ረገድ ሙሉና እኩል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ፣ ማሳደግ እና ለዚህም ጥበቃ ማድረግ ይገባል፡፡
የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እኩል ዕድል ይበልጥ ይረጋገጥ ዘንድ በብሔራዊ፣ በአህጉራዊም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ወጥተው በሀገራችን እየተተገበሩ ያሉ ፖሊሲዎችና ህጎችን አውቆና በአግባቡ ተረድቶ ተግባረዊ ማድረግ ለአንድ አስፈፃሚ አካል የሚተው አይደለም፡፡ በየአካል ጉዳት አይነቱ ካለው ጥያቄና ከተግባሩ ስፋት አንፃር ሥራው ሰፊ በመሆኑ ቁርጠኝነትና ውጠየታማ የቅንጅት ሥራን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን መብቶች መሰረት አድርጎ በመስራት ረገድ ሁሉም ባለቤት ሆኖ አካቶ ሊሰራው ይገባል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሁሉም የራሴ ጉዳይ ነው በሚል ወስዶ በመፈፀም አካል ጉዳተኞች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በእኩል ደረጃ በማህበረሰቡ ውስጥ ሙሉና ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚገድቡ መሰናክሎችን በጋራ ለመቅረፍ ህጎቹን ተግባራዊ ማድረግ የሁሉንም ቁርጠኛ ወገንተኝነት ይጠይቃል፡፡
በተቋም ደረጃ ከተሰጠ ኃላፊነት አንፃር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ምን ያህል ተተግብሯል የሚለውን መመልከት ይገባል፡፡ ሁሉም ሴክተር የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በአግባቡ እንዲተገበሩ ሊሰራ ይገባል፡፡ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 የአካል ጉዳት እክል ያለባቸው ዜጎች የአካል ጉዳት ከሌላቸው በእኩልነትና በፍታሀዊነት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ፤ ሊከበርላቸው የሚገቡ መብቶችን አስቀምጧል፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ሥር ሰዶ የቆየው ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ በአካ ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ቀደም ሲል በሥራ ላይ የቆየውም የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብት አዋጅ ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተገቢውን የህግ ከለላ የማይሰጥ ሆኖ በመገኘቱ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 እንደወጣ መነሻ ምክንያት ሆኖዋል፡፡
በ2000 ዓ.ም ወጥቶ በስራ ላይ ያለው አዋጅ በሚለው ልክ በተፈፃሚነት ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው ለአመታት ስራ ላይ የቆየውን የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ዛሬም መለስ ብለን እንድንቃኝ እና የፈፃሚ አካላትን ትኩረት እንድንኮረኩር አድርጎናል፡፡
ኢትዮጵያ ከምትከተለው እኩል የሥራ እድል መርሆ ጋር የሚጣጠም፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታ የሚፈጥርና በሥራ ስምሪት መብት ቁጥር 568/2000 በ2000 ዓ.ም ወጥቶ ስራ ላይ ውሎዋል፡፡ አዋጁ በማነኛውም ሥራ ፈላጊ አካል ጉዳተኛ ሠራተኛና በአሰሪ መካከል በሚኖር የሥራ ስምሪት ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ ነው፡፡
የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት መብትን ለመጠበቅ የሥራው ጠባይ የማይፈቅድ ካልሆነ በስተቀር በውድድር ብልጫ ነጥብ ያገኘ ማንኛውም የአካል ጉዳተኛ በምንም ዓይነት መልኩ መድሎ ሳይደረግበት የሥራ እድሉን በቅጥር፣ በድልድል ወይም በዝውውር መያዝና በሀገርም ይሁን በውጭ የሥልጠና እድል የማግኘት መብት አለው፡፡
በውድድር ውጤት እኩል ወይም ተቀራራቢ ነጥብ ያገኘ ማነኛውም የአካል ጉዳተኛ በምንም ዓይነት መልኩ መድሎ ሳይደረግበት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በስራው አስገዳጅነት ካልሆነ በስተቀር ማነኛውም የመወዳደሪያ መስፈርት በተወዳዳሪው ላይ ያለውን ጉዳት የሚመለከት መሆን የለበትም፡፡ ማንኛውም የአካል ጉዳተኛ የተመደበበት የሥራ መደብ የሚያስገኘው ደመወዝና ሌሎች ጥቅሞችን የማግኘጥ መብት አለው፡፡
የአካል ጉዳተኛ እኩል የሥራ ዕድል የሚያጣብብ፣ ሕግ፣ አሠራር፣ ልማድ፣ ዝንባሌ ወይም መድሎ የሚፈጥር ሌላ ሁኔታ ሕገ-ወጥ መሆኑ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡ ለሥራ ስምሪት የሚቀመጡ መስፈርቶች የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ዕድል የሚያጣብቡ ሆነው ከተገኙ፤ ተመጣጣኝ የሆነ ምቹ የሥራ ሁኔታ ባለመፈጠሩ የአካል ጉዳተኛው በዕኩል የሥራ እድል መብቱ መጠቀም ባለመቻሉ የሚፈጠር የሥራ ዕድል መድሎ እንደመፈፀም ይቆጠራል፡፡
የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ለአካል ጉዳተኞች የሰጣቸውን መብቶች አዋጁ ባስቀመጠው ልክ ተረድቶ መፈፀም የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ አካታችና ዘላቂ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አለም ለመገንባት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ጉዳያችን አርገን መቀበልና አካል ጉዳተኞችን ተመልክቶ የወጡ ፖሊሲዎችንና የህግ ማእቀፎችን ተረድተን ለመተግበት ቁርጠኛ ሆነን ልንነሳ ይገባል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶችን ተፈፃሚ ማድረግ ለማንም የምንተወው ጉዳይ አይደለም!!
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *