ኢትዮጵያ ዜጎቿን ትሰበስባለች፤

ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመስራት መብታቸውን የምታከብር ለዜጎቿ ውድ፤ ዜጎቿ ለሷ ውድ የሆኑት ኢትዮጵያ ሁሌም ከዜጎቿ ድምጽ አትርቅም፡፡ የዜጎቿ ደስታ ደስታዋ፤ የሷ ሰላምና ብልጽግና ለዜጎቿ ደስታቸው፤ እንዲህ ነው ትስስራቸው፡፡ ከዚህም በላይ ነው ህዝቦቿ ብዙ ለዋለችላቸው ሀገር ፍቅራቸው፡፡
ሀገር በውለታ ባትለካም ያላትን ሳትሰስት የምትሰጥ እናት ናት ኢትዮጵያ፡፡ በተለያየ ምክንያት በአካል እንጂ በመንፈስ ያልራቋት ልጆቿን የምትናፍቅ፡፡ ልጆቿን የማትጠግብ፣ አንዱን ከአንዱ ልጇ የማትለይ የእናት ምሳሌ የሆነች ውድ ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ሲከፋ የምትተው ሲለማ የምትሻ ሀገር ሆና አታውቅም፤ ህዝቧ አንጀቱ ለሀገሩ እንዲህ አልተሰራም፡፡ በአካል የራቀው ወገን ሀገሩን ከልቡ አውጥቷት አያውቅም፣ ተግባር ምስክር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገር ወደ ቀድሞ ከፍታዋ ተመልሳ ማየት ነው ህልማቸው፡፡ ከማድረግና ከማግኘት በላይ ነው ኢትዮጵያና ህዝቧ፤ ህዝቧና አትዮጵያ የተጋመዱበት ገመድ ስሪቱ፡፡
የዜጎች ህመም ህመሟ፤ የሷ ህመም ለዜጎቿ ስቃይ የሚሆንባት ኢትዮጵያ የአቅሟን ሳትሰስት ታደርጋለች፡፡ ያላትን ሳትቆጥብ፣ የቻለችውን ሳትገድብ የምታደርግ ኢትዮጵያ ትላንትም፣ ዛሬም በሰው ሀገር በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቿ ስትል ትታመማለች በቻለችው ሁሉ ትደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያና ህዝቧ የተጋመዱበት ገመድ የማይፈታ፣ የማይበጠስ ነው፡፡ ችላ ችላ የማትል ሀገር፤ ችሎ እርቆ የማይለያት ህዝብ ያላት፤ አይደለም ለዜጋዋ ለእንግዳ የሚትረፈረፍ ፍቅርን የምትቸር ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
ኢትዮጵያ ሁሌም ከዜጎቿ ድምጽ አትርቅም እናት ይህን ለማድረግ ሆኖላት አያውቅም፡፡ በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቿ ድምጽ ከሀገር በላይ ከፍ ብሎ የሚሰማው አይገኝም፡፡ ስስት ሳይሆን አቅም ሩጫዋን ቢገድብም ለልጆቿ ሳትደርስ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን አትቀርም፡፡
በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ለመመለስ የዜጎቿን ድምጽ ከማዳመጥ የማትዘናጋው ኢትዮጵያ ዛሬ ደርሳለች፡፡
ዜጎቿን ልትቀበል ተሰናድታለች፡፡ በአካል የራቋት ልጆቿን ሁሌም በናፍቆት የምትጣራው ሲመጡ በፍቅር የምትቀበለው ኢትዮጵያ ዛሬም በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቿን ለመሰብሰብ አቅሟን አሰባስባ ተነስታለች፡፡ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማምጣት፣ አምጥታም ለማቀፍ እናት ሀገር የፍቅሯን፣ የዜጋ ክብሯን ታደርጋለች፡፡
የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አይደለም ለዜጎቿ ለሰው ዘር በሙሉ ጀርባዋን አትሰጥም፣ አይደለም ህዝቧን የሰው ዘርን ማቀፍና መቀበል ለሷ ግብሯ ነው፡፡ ዜጋዋም እንደዛው… ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ተስፋ ቆርጦ አያውቅም የኢትዮጵያ ብቃይ ነውና ከሀገሩ ፍቅርን ወርሷል፡፡ አይደለም ያለውን ተፈጥሮን አጋርቶ አብሮ መኖርን ተፈጥሮ በሰጣት ሀብት ከኢትዮጵያ ተምሯል፡፡
በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር በማምጣት የስነልቦና ድጋፍ አገልግሎት በመስጠትና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተለያዩ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት መንግታዊ ተቋማት ድርሻቸውን ወስደው ኃላፊነታቸውን መወጣት ጀምረዋል፡፡
የማቆያ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት ከፌደራል እስከ ክልል ዜጎች ተገቢው አቀባበል ተደርጎላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
በዚሁም መሰረት ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከሳውዲ አረቢያ ወደሀገራቸው የመሚመለሱ ዜጎችን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵውያን በፍቅር መቀበል ይጀምራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከናፈቀው ቤተሰቡ ጋር ይገናኛል፡፡ በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ ቆይቶ የመጣ ወገንን ያለፈውን ህመም የሚያስረሳ አቀባበል ማድረግ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ሁሉም ዜጋ ተመላሽ ወገኑን በፍቅር በመጎብኘት እና ከጎኑ በመቆም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ትሰበስባለች፤ እንግዳ ተቀባይ ህዝቧም ልጆቹን ያቅፋል!!!
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *