“ደግ ልቦች – ከውብ ፊቶች ይበልጣሉ!!”

በርካታ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር እንደገጠማቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢታይባቸውም ታማሚነታቸውን አምነው ለመቀበልና ለችግራቸው መፍትሄ ለመፈለግ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

አዕምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት ሊዳረግና የተለመደ ተግባሩን መወጣት ሊሳነው ይችላል፡፡ ለአዕምሮ መታወክ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ማህበራና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ሥነልቦናዊ ውጥረቶች ፣ስደት ፣ጦርነት ፣ ተገዶ መደፈር፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የመኪና አደጋ፣ ኢንፌክሽን አምጪ በሽታዎችን አለመቆጣጠር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎችን የማያማክሩ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ቁጥር ማነስና ስለ አዕምሮ ህሙማን ዜጎቻችን ያለን ግንዛቤ አነስተኛነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በሃገራችን በአዕምሮ ህመም ላይ የተሰሩ ጥናቶች ጥቂት ቢሆኑም ከ6 ሰዎች አንዱ በህይወት ዘመኑ ለአዕምሮ ጤና መቃወስ እንደሚጋለጥ ያመለክታል፡

የሚያሳዝነው ደግሞ ከ90 % በላይ የሚሆኑት የአእምሮ ህሙማን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ውሱንነቶች ተጋላጭ ናቸው፡፡ይህ ማለት ደግሞ ሁላችንም በማንኛውም ጊዜ ለአዕምሮ ጤና ችግር ልንዳረግ እንደምንችል በመረዳት የአእምሮ ህሙማን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ሽፋንን ለማስፋት በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረቶች ላይ ልንረባረብ እንደሚገባ ልብ ይሏል፡፡

በቅርቡ “ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት -ትርጉም ያለው ትብብር!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ቢሮ አዘጋጅነት በሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት ዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀንን በማዕከሉ ለሚገኙ የአእምሮ ህሙማን ጋር ፣ በዓሉን በጋራ ለማክበር ችለናል፡፡
ማህበሩ በአንድ ግለሰብ ተነሳሽነት በሽንቁሩ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በ2008 ዓ.ም ተመስርቶ በአሁን ሰዓት በእንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ወ/ኤልያስ ይዞታ የሆነውን ቦታ በመከራየት በርካታ ህሙማን ከጎዳና ላይ በማንሳት የስነ ልቦና ድጋፍ፣ የህክምና ድጋፍ፣ መጠለያ፣ አልባሳትና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የአእምሮ ህሙማኑ ሲሻላቸውም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ በማሰማራት ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ ሲሆን በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ህሙማን ከቀን ወደ ቀን በለውጥ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በአዕምሮ ህመም፣ በረሀብ፣ ደጋፊ በማጣት ምክንያት ወደ ማዕከሉ ያስገባቸውን ህሙማኖች በሚያደርግላቸው እንክብካቤ ፣ ድጋፍና ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ የጤና ለውጥ እንዲያመጡ በትጋት በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን የጤና ለውጥ ያመጡ ህሙማኖችን ከስነ-አዕምሮ ባለሙያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ከገቡበት የአዕምሮ ህሙማን ተግዳሮቶች ፈጥነው እንዲወጡ የሚያስችል ተልዕኮ ሰንቆ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

follow and like Ministry of Women and Social Affairs
error
fb-share-icon
Tweet

በማህበሩ ማዕከል በነበረን ቆይታና በጉብኝታችን ወቅት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ለገሰ እንደነገሩን ማህበሩ በሚያደርግላቸው እንክብካቤ፣ ድጋፍና ህክምና ወደ ቀድሞ ጤናቸው የተመለሱ ህሙማኖችን ከተለያዩ የሙያ ተቋማት እና ማህበራት እንዲሁም ግለሰቦች ጋር ትስስር በመፍጠር የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ስራ አስኪያጁ አክለውም ከማህበሩ በሚያገኙት ስልጠናም ሆነ ድጋፍ የተለያዩ ሙያዊ የስራ እድሎችን አግኝተው የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በሚሠሩባቸው ዘርፎች ራሳቸውንም ሆነ በዙሪያቸው ያሉ ወገኖችን እንዲጠቅሙ ማድረግና በህይወታቸው ውስጥ ለብዙዎች አርአያ የሚሆኑበትን ዕድል እንዲፈጠር ማስቻል የሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር አላማ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡

የሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር ዕሴቶች – ግልፅነት፣ ቅንነት፣ የላቀ አገልግሎት መስጠት፣ በዕውቀትና በእምነት መመራት ፣ ያለ አድሎ ድጋፍ ማድረግ መሆናቸውን የገለጹት ስራ አስኪያጁ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በእንጦጦ ቅዱስ ራኤል በተክርስቲያን ይዞታ የሆነውን ቦታ በመከራየት ከ320 በላይ የሚጠጉ ህሙማን በመርዳት ላይ ከመሆናቸው ባሻገር ጤናቸውን በቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ አማኑኤል ሆስፒታል እንዲሁም አጋር ከሆኑ የተለያዩ ሆስፒሎች ጋር በጋራ በመሆን ክትትል ማድረግ ፣ ወደ ማዕከሉ ገብተው የዳኑ ህሙማን ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ፣ራሳቸውን እንዲችሉና በዕድሜ የገፉትን አረጋውያንን በማዕከሉ ዘለቄታዊ እንክብካቤ እና ድጋ

ፍ እንዲያገኙ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በዚህ መሰረት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ሴቶች ህጻናት ወጣቶች አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዘላቂና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አንጻር የሰሊሆምንና ሌሎች አርዓያነት ያላቸው የማህበራት ተልዕኮ በመጋራት በቅንጅት፣ በባለቤትነትና በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በመጨረሻም ህሙማኑን ለመርዳት ሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን በመጎብኘት፣ ለህሙማኑ ፍቅር እና እንክብካቤ በመስጠት፣ ልብሳቸውንና ገላቸውን በማጠብ፣ ከገቡበት የጤና መጉደል በመታደግና ከህሙማኑ ጋር በጋራ በመመገብ ለነሱ ያለንን ወገናዊ ፍቅር በመለገስ እንዲሁም ባለን አቅም በገንዘብ በመርዳት፣ በጉልበት በማገልገል፣ በእምነት በማበርታትና በፍቅር ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ እንትጋ መልዕክታችን ነው፡፡

በዓለማየሁ ማሞ

ምንጭ – ከሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር የህትመት ውጤቶች

Please follow and like us: