የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር በመቀሌ ዙሪያ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ294.9 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

ገንዘቡ ከአለም ባንክ የተገኘ ድጋፍ ሲሆን በመቀሌ ዙሪያ ለሚገኙና ለችግር ተጋላጭነታቸው በክልሉ አግባብነት ባለው አካል ለተመረጡ 68,855 ተፈናቃዮች የሚተላለፍ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በተለያዩ ምክንያቶች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባት፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም እንዲሁም ከሳውዲ ዓረቢያ በበርካታ እንግልትና ጭቆና ውስጥ ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲጥሩ የነበሩ ዜጎቻችንን ወደ እናት አገራው በመመለስ መልሶ ማቋቋምና ድጋፍ ለማድረግ በመንግስት በኩል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ በመቀሌ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች አንፃር ድጋፉ በጣም ትንሽ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የተደረገው ድጋፍ የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑት ቅድሚያ በመስጠት በፍትሃዊነት እንዲዳረስ የሚመለከታቸው አካላት በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የመቐለ ከተማ ምክትል ከንቲባና የፐብሊክ ሰርቪስ ሃላፊ ኤልያስ ካሕሳይ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በክልሉ ለሚገኙ የሚመለከታቸው መ/ቤቶች ባለሙያዎች ስልጠናም ተሰጥቷል።

ዘጋቢ ስለእናት እስክንድር

Please follow and like us: