የአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) በአረንጓዴ ልማት እና ሴቶችን በማብቃት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውና ድጋፍም እንደሚያደርግ አስታውቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) ምክትል ጀነራል ዳይሬክተር ሚስስ ሄሌና ማክሌዮድ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር እና ሴቶችን ማብቃት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

በዚሁ ወቅትም፥ ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሴቶችን በገንዘብና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራትና በልማት ህብረት በማደራጀት መብታቸውን ማስከበር እና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ እንዲችሉ በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርም ሴቶች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑንና በዚህም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማት ተግባራት ከ13ቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም አንዱ የስራ ስምሪት መስክ መሆኑንና በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶች በተለይ በችግኝ ተከላና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙና ወጤቱንም በተጨባጭ መመልከት መቻሉን አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ብሎም ሴቶችን ለማብቃት እንደሀገር የሚካሄዱ ሰፋፊ ኢንሼቲቮች መኖራቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመው GGGI ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) ምክትል ጀነራል ዳይሬክተር ሚስስ ሄሌና ማክሌዮድ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየዘርፉ እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

በቀጣይ በተለይ በአረንጓዴ ልማት እና ሴቶችን በማብቃት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና ድጋፍም እንደሚያደርጉ በውይይቱ አስታውቀዋል።

Please follow and like us: