የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሬክስሩ ትሬዲንግ አ.ማ ድርጅት ጋር የለውጥ ትውልድ የተሰኘውን ፕሮጀክትን በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈፀመ።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በስነስርአቱ ላይ እንደገለጹት ወጣቶች የመሪነት ሚናቸውን እንዲያጐለብቱ እና ንቁ ተሳታፊ በመሆን አቅም እና ብቃታቸውን እንዲጎለብት እንዲሁም የአገር ወዳድነት ስሜታቸው እንዲያድግ ለማድረግ በቅድሚያ በመልካም ስብዕና የታነጹ እንዲሆኑ በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር በቅረበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

ሚኒስትሯ አክለውም ሃገራችንን ወደ ብልጽግና ጉዞ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት የወጣቶችን አስተሳሰብ በማልማት የለውጥ ትውልድ መፍጠር ዋነኛ መንገድ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተከታታይነት ያላቸው የስብዕና ልማት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ የልቦና ውቅርን የሚያስተካክሉ ስልጠናዎች መስጠትም ሀገራችን ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ አስፈላጊነቱን አብራርተዋል። እነዚህን ስልጠናዎችና መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከብሬክስሩ ትሬዲንግ አ.ማ ጋር በመተባበር እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የብሬክ ስሩ ትሬዲንግ (break through trading) የቦርድ ስብሳቢ አቶ ነጻነት ዘነበ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማው በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት ስብዕናቸው የታነጸ፣ ህይወታቸው የተለወጠ፣ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ማብቃት መሆኑን አመላክተዋል።

 

ስልጠናው በቀጣይ 8 አመታትም በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር መሆኑን እና 20 ሚሊዮን ወጣቶችን እና 10 ሺህ ወጣቶችን ደግሞ በአሰልጣኞች ስልጠና ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን በመድረኩ ተገልፅዋል።

ዘጋቢ ስለእናት እስክንድር

Please follow and like us: