በአንድነት መቆምና መረዳዳት ከተቻለ የዘመናት የኢትዮጵያ የሴቶችን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዳ ጠንካራ መሠረት መጣል ያስችላል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

“ትብብር ለለውጥና የጋራ ንቅናቄ ለመገንባት” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ሴቶች ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሃገራችን በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያ ሴቶች  እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ የሴቶች መብቶችን ለማስጠበቅና የሚገጥማቸውን የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አያሌ ትግል ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡የሴቶችን ጥያቄዎች ወደ ሚመለከታቸው ውሳኔ  ሰጪ አካላት እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ  ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ትኩረት እንዲሰጠው በርካታ ስራዎች መሠራቱን ገልጸዋል፡ ፡

ባለፉት አመታትም በመንግስት የተወሰዱ የህግ፣ የፖሊሲ፣ የመዋቅርና የአሰራር ማሻሻያዎችና ፕሮግራሞች በሃገራችን የሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራና በፖለቲካው ዘርፍ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሁሉም የሀገራችን ሴቶችን ጥያቄና ፍላጎት ማዕከል ያደረገና የጋራ ድምጽ ሆኖ የሚያገለግል ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ የሴቶች ምክር ቤት ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

በአንድነትና በህብረት መቆምና መረዳዳት ከተቻለ የዘመናት የኢትዮጵያ ሴቶችን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዳ ጠንካራ መሠረት መጣል እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች ህይወት ላይ ትርጉም ያለውና አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም በሴቶች አደረጃጀቶች በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደፊትም ድጋፋን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገ/መድን በበኩላቸው እንደሀገር ለውጦች መኖራቸውን ገልጸው በመንግስትና አጋር አካላት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። ኮንፈረንሱ የተቀናጀና በስርዓት የተደገፈ፣ ንቁና ውጤታማ እንቅስቃሴ ለማካሄድና የተጀመረውንም ንቅናቄ ለማጠናከር የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በኮንፈረንሱ ላይ የተለያዩ በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶችና አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

ዘጋቢ መላኩ ባዩ

Please follow and like us: