የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራውን ስራ እገዛ ማድረጉን አስታወቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር እና በኢትዩጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን ከሆኑት አቢባቱ ዋኔጋር ተወያይቷል።

በዉይይቱ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ከነዚህም ተግባራት መካከል መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስና ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚንስትራ አክለውም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከምንጩ መካላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎች እና ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እንድትሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል ።

ተመላሽ ዜጎች በተለይም ወላጆቻቸውን በስደት ላጡ ህፃናት፣ ሴቶች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ እና ዘላቂ የሆኑ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሯ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያና በዜጎቿ ላይ እያስከተለ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ካሉ ተቋማት ጋርም በትብብርና በቅንጅት መስራቱንም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የየዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር በበኩላቸው ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም እያደረገች ያለችውን ጥረት አድነቀው፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ኢትዮጵያ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራውን ስራ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ።

Please follow and like us: