መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ከሀገር ወጥተው የነበሩ 180ሺ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል። የንቅናቄ መድረኩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ህብረት ለመፍጠር ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት በአንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከሀገር ወጥተው የነበሩ 180ሺ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። በሌሎች ሀገሮች በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ክብርት ሚንስትር ዴኤታዋ  መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ተጎጂ የሆኑ ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምና ለዳግም ስደት እንዳይጋለጡ የማድረግ ስራ  ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልፀዋል ::

በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይና የመልሶ ማቋቋም ክላስተር ሴክሬታሪያት ሃላፊ ጄነራል ተክላይ አሸብር በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የወጣቶች ፍልሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ችግሩ ለመከላከል መድረኩ ወቅታዊ መሆኑን ተናግረዋል። በሱዳንና በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ እንዲሁም የጂቡቲንና የየመንን በረሃዎችና ባህር በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሀገራት በሚያደርጉት ጉዞ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ በመድረኩ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ችግሩን ለመቅረፍ መሰረታዊ መፍትሄ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

በመድረኩ ከፌደራል ፣ከአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅትና ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተውጣጡ በየደረጃው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ታድመዋል።

ዘጋቢ ስለእናት እስክንድር

Please follow and like us: