በተቋሙ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲከናወኑ  በተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም ዙሪያ ከፌዴራል ተቋማት ከተውጣጡ የሱፐርቪዝን ቡድን አባላት ጋር ውይይት ተካሄደ ።

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያከናውናቸው በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም ዙሪያ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ከተገኙ የሱፐርቪዝን ቡድን አባላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ የሱፐርቪዥን  ቡድኑ በተቀናጀ አግባብ የተከናወኑ ተግባራትን በጋራ ለማየት ትኩረት መሰጠቱን እንደሚያደንቁና የሚሰጠውም ግብረ መልስ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች አጋዥ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሱፐርቪዝን ቡድኑ ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲተዩት የተውጣጡ አባላት ያቀፈ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወጣቶችና ማህበራዊ ዘርፍ  በተለይ ከወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከወጣቶች ስብእና ልማት ግንባታ እና አረጋውያንን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ከመደገፍ አንጻር የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት አድምጧል።

የቀረቡትን ስራዎች ከመረጃ ተኣማኒነት፣ ከበጀት፣ ከጥናትና ምርምር፣ ከአመላካቾች ምዘና፣ ከመዋቅር፣ ከመረጃ ስርዓት ግንባታ፣ ከፖሊሲና ህግ ማዕቀፎች፣ ከክትትል፣ ግምገማና ሱፐርቪዝን ስራዎች፣ ቅንጅታዊ ስራን ከማጠናከርና ተጠያቂነት ከማረጋገጥ፣ ሀብት ከማሰባሰብ፣ ግንዛቤና ስልጠና ከመስጠት እንዲሁም ማሳያ ሊሆን የሚችል ተጨባጭ ማስረጃ ከማቅረብ አንጻር ተጨማሪ ገለጻ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ማብራሪያ እንዲሰጥበት በሱፐርቪዥን ቡድኑ ተጠይቆ ከአቅራቢዎች እና ከተሳታፊዎች ምላሽና ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ከሪፖርት በተጨማሪም የመስክ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን በዋናነትም ሞዴል የወጣት ማዕከልን፣ በወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተገነቡና የታደሱ ቤቶችን፣ ብሔራዊ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ቦታንና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በተለይ ከጎዳና ላይ የተነሱ ዜጎችን የተሃድሶ ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው ምርታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ታስቦ አለም ባንክ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀውን የማገገሚያ ማዕከል በአካል በመገኘት መመልከት ተችሏል።

በመጨረሻም ሱፐርቪዥን ቡድኑ ሪፖርቱንና የመስክ ጉብኝቱን መሠረት በማድረገ የማጠቃለያና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የዕለቱ መርሀ ግብር ተጠናቋል።

 

Please follow and like us: