የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከሳአውዲ ተመላሽ ዜጎች የሚገኙበትን ማቆያ ማዕከል ጎበኙ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ሚንስትር ድኤታዎች በዛሬው ዕለት ከሳአውዲ ተመላሽ ዜጎች በማቆያ ማዕከላት የሚደረገውን ድጋፍ እና እንክብካቤ በአካል በመገኘት ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ዜጎች መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በምንም አይነት ሁኔታና አማራጭ ማድርግ የለባቸውም፡፡ መንግስት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለማስቀረትና ዜጎች ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ተዘዋውሮ የመስራት መብታቸው ተጠብቆ ከሀገር ውጪ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸቱ ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ከነዚህም ተግባራት መካከል መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስና ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። የዚህም አንዱ አካል መደበኛ ባልሆነ መልኩ ወደ ሳአውዲ አረቢያ በተለያየ ጊዜ የሄዱ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ ከአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች አለም አቀፍና ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡

ሚንስትሯ አክለውም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከምንጩ መካላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎች እና ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እንድትሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል ። ተመላሽ ዜጎች በበኩላቸው በማዕከሉ የህክምና የምግብና የመጠለያ አገልግሎቶችን እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን አሁንም መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታና ወደ ትውልድ ቦታቸው ከመመለስ ጋር ተያይዞ አንዳንድ መዘግየቶችና ሌሎች ድጋፎችን በበቂ ሁኔታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ ከ7000 በላይ ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተችሏል።

 

Please follow and like us: