የቤተሠብ ቀን ቢትዮጵያ ለ2ኛ ጊዜ መተሳሰብ እንደ ቤተሰብ ለሀገር እና ለማህበረሰብ !!! በሚል መሪ ቃል ተከበረ፡፡

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያረጉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚንስትር ድኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ዑመድ እንደገለፁት ቤተሰብ የራሱን እና የአባላቱን ደህንነት በመጠበቅ ለጤናማ ሀገርና ማህበረሰብ ምስረታ መተኪያ የሌለው እና ወሳኝ መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አክለውም የቤተሰብ አባላት ደህንነት በመልካም ሥነ-ልቦና፣ በአካላዊ ጤንነት እና በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥ ሲሆን የቤተሰብ ተቋም ለሁሉም ነገር ቀዳሚ ለሁሉም ነገር መነሻ ነው፡፡ ሚኒሰትር ድኤታዋ እንደገለፁት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረትም ቤተሰብ እንደ ህብረተሰብ መሰረትነቱ ተገቢ ሚናውን መወጣት እንዲችል፤ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መብቶቹ እንዲጠበቁ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን እንዲቋቋም፣ መልካም እሴቶቹ እንዲጠበቁ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል የሥራ ክፍል በማደራጀት የሠው ኃይል በመመደብ እና ክልሎች እና ባለድርሻ አካላትም በተመሳሳይ ሚናቸውን መወጣት እንዲችሉ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የዘንድሮው የቤተሰብ ቀን‹ መተሳሰብ እንደ ቤተሰብ፣ ለሀገርና ለማህበረሰብ› በሚል መሪ ቃል የተከበረበት ዋና አላማ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ጠቀሜታዎችን፣ የመቀራረብ እና በጋራ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ የመግባባት አስፈላጊነቶችን፣ በቅንጅት የመስራት እና ለሌሎች በበጎ መንገድ ዋጋ የመክፈል እሴቶችን የሚቀሰቅስ እና የሚያሰታውስ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል ።

የቤተሰብ ቀን ዓላማ ቤተሰብ እንደ አንድ ወሳኝ ተቋም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተገቢ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል የሚያግዙ ግንዛቤዎችን ለህብረተሰቡ እና ለባለድርሻ አካላት መፍጠር እና የትኩረት አቅጣጫዎችን ማመላከት ነው። በመድረኩ ላይ ለአንድ ዓመት የሚቆይ እና ሁሉንም ቤተሰብ በተለያዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ እቅድ ይፋ የተደረገ ሲሆን ክልሎችም በዚሁ አግባብ ተፈጻሚ እንዲያደርጉት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Please follow and like us: