በጎ አስተሳሰብ – በጎ አስተዋጾአችንን የምናበረክትበት ተጠባቂው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት!

በጎ ፈቃደኝነት በዓለም ዙሪያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ታላቅ ተግባር ነው። በችግር እና በድንገተኛ ጊዜ፣ በፈተና እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ ግንባር ቀደም ደራሾች በጎ ፈቃደኞች ናቸው። ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ተግዳሮቶች በገጠሟትና በሚገጥሟት ጊዜ፣ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በጎ ፈቃደኞች የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ሁሉም ሰው በጎ ፈቃደኝነት ቢያዘወትር ዓለም ለሰው ልጅ ሁሉ የተሻለ ስፍራ ትሆን ነበር የሚባለው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከማህበረሰባችን የአኗኗር ዘይቤ፣ ከሃይማኖት፣ ከባህል እና ከእምነት አስተምርሆ ጋር በጥብቅ የተቆራኘና በደስታ፣ በሀዘንና ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሲከሰቱ የመረዳትና የመደጋገፍ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው መልካም ተግባር ነው፡፡ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የክረምትና የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች ተቀርጸው ለማህበረሰቡ በተደራጀ መንገድ የተለያዩ አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም ወጣቶችን ጨምሮ ዜጎች ለማህበረሰባቸው ብሎም ለሀገራቸው በጎ አስተሳሰባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን እንዲያበረክቱ በማድረግ የልማት ክፍተቶችን መሙላት አስችሏል።

እየተካሄደ ያለው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለበጎ ስራ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች ወገናቸውን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰናይ ተግባራትን ማከናወን የሚችሉበትን ዕድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ከማህበረሰባቸው ጠቃሚ ባህልና እውቀት እንዲቀስሙ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል። ለአብነትም እንኳን ከ2011ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 5 ዓመታት በስምሪት መስኮችም ሆነ በተሳትፎና ተደራሽነት ረገድ በዘርፉ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል። የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር በ2011 በጀት ዓመት ከነበረበት 11ሚሊዮን ወደ 24 ሚሊዮን እንዲሁም የተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ብዛት ከነበረበት 19ሚሊዮን ገደማ  ከ56ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

የተሰጠው አገልግሎት በገንዘብ ሲተመንም ሲጀመር ከነበረበት ከ5ቢሊዮን ብር ወደ 17ቢሊዮን ብር በላይ ማደግ ችሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው አሁንም ወደፊትም በቅንነት ተነሳስተን ከተባበርንና በትጋት ከሰራን ችግሮቻችን ደረጃ በደረጃ መፍታትም ሆነ በዘላቂነት መቅረፍ የሚያስችል እምቅ አቅም በእጃችን ላይ ያለ መሆኑን ነው። እናም ይህን አቅማችንን አቀናጅተን በምልዓት  ልንጠቀምበት ይገባል። ተጠባቂው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሁን ላይ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ሀገራዊ እቅዱን መነሻ ያደረገ እንቅሰቃሴ በየአካባቢው እየተጀማመረ በመሆኑ ከአምናው በተሻለ በጎ አስተሳሰብና በጎ አስተዋጾአችንን ማበርከትም ሆነ እምቅ አቅማችንን መጠቀም የምንችልበት ዘንድሮም ሌላ ዕድል አለን  ። ታዲያስ እርስዎ እንደአንድ በጎ ቅን አሳቢ ዜጋ ላሉበት ማህበረሰብ፣ ለሚኖሩበት አካባቢ እና ለእናት ሀገርዎ ምን ለማበርከት ተዘጋጅተዋል? የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትንሸ የለውም። ይነስም ይብዛም የእርስዎ አስተዋጾዖ ለውጥ ያመጣልና ከቅን ልቦና በመነጨ ለመልካም ስራ ዘወትር ይተባበሩ። ይጀግኑ፥ የድርሻዎን እየተወጡ የበጎ ፈቃድ አርበኛም ይሁኑ መልዕክታችን ነው።

Please follow and like us: