በየአካባቢው ያሉትን ሃብቶች በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት መላቀቅ ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

በየአካባቢው ያሉትን ሃብቶች በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ  የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሐረሪ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ነው። ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር ) መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በክልሉ በቀላሉ ሀብት ሊያስገኙ የሚችሉ ፀጋዎች መኖራቸውንና ያሉትንም ሃብቶችን በመጠቀም ህብረተሰቡ እያከናወናቸው የሚገኙት ስራዎች አበረታች ናቸው። በተለይም አርሶ አደሩ ባለው አነስተኛ መሬት ላይ እያከናወነ የሚገኘው የአትክልትና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ውጤት ማምጣትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻላቸውን የኢዜአ ገለጻ ያመለክታል።

ወጣቶችም ከስራ ጠባቂነት ይልቅ በሌማት ትሩፋት ስራ ፈጥረው መንቀሳቀሳቸው ገቢ ማግኘት እንዲችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል። በአብሮነት መስራት ልምላሜንና ሃብትን የሚያጎናጽፍ መሆኑን በክልሉ በመስክ ምልከታ ወቅት ማረጋገጥ መቻሉንም ተናግረዋል። እንዲሁም በየአካባቢው ያሉትን ሃብቶች ባግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጆክ “ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ” የተዘጋጀ የማስፈፀሚያ ጽሁፍ ለውይይት እያቀረቡ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

 

Please follow and like us: