ሀገር አቀፍ የህጻናት ፓርላማ በይፋ ተመሰረተ

መጪውን የሀገራችንን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ራእይ ሰንቀን እንጓዛለን ሲሉ ተመራጩ የሀገር አቀፍ የህጻናት ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ገለጹ
የሀገራችንን ህጻናት ሁለንተናዊ መብቶችንና ጠቅሞችን ለማረጋገጥ እንዲያስችል ሀገር አቀፍ የህጻናት ፓርላማ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ ተመሰረተ፡፡ ከ10 ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 132 አባላትን ያቀፈው አዲሱ የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ ዛሬ በይፋ ሲመሰረት የተከበሩ ተማሪ ቅዱስ ሞላን የፓርላማው አፈ-ጉባኤ ፣ የተከበሩ ተማሪ እህተመድህን አበባውን ምክትል አፈ-ጉባኤ እንዲሁም የተከበሩ ተማሪ ሶስና ዘለቀን ጸሀፊ አድርጎ መርጧል፡፡
በምርጫው ስነ-ስርአት ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የህጻናት ታዛቢዎች፣ ከሁሉም ክልሎች የመጡ የህጻናት ፓርላማ አባላት፣ የሲቪክ ማህበራትና የአለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ የህጻናት ፓርላማ ምስረታ ላይ ተገኘተው ለህጻናቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት የህጻናት ፓርላማ መመስረቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለበትና በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገኝ ከማድረጉም በላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህፃናት ፓርላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለህጻናት መብትና ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በእለቱም በከፍተኛ ድምጽ የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሆነው የተመረጡት ተማሪ ቅዱስ ሞላ እንደገለጹት መጪውን የሀገራችንን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ሁሉንም የህጻናት ፓርላማ አባላትን በማስተባበር ራእይ ሰንቀን እንጓዛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በቆይታቸውም ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመጡት የህጻናት ፓርላማ አባላት ስለሀገራችን ተፈጥሮ፣ታሪክ፣ወግና ባህል በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ለማስቻልና የእርስ በእርስ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ቤተመንግስት የሚገኘውን የአንድነት ፓርክ ጎብኝተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያም የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ህጻናት በጦርነቱ ምክንያት ከአማራና ከአፋር ክልሎች ተፈናቅለው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት ድጋፍ እንዲሆን አስር ሺህ ብር ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አስረክበዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *