ለሁት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የማህበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ በስኬት መጠናቀቁ ተገለፀ

(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/ 2015 ዓ.ም) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የማህበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ ዓላማውን ማሳካቱንና እንደሀገር በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለመገንባት የማያስችሉ ጠቃሚ ግብዓቶች እንደተገኙበት ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ያለፉት ሁለት ቀናት በርካታ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እና በሃገራችን የማህበራዊ ጥበቃ ያለበትን ደረጃ በቀረቡት ፅሑፎች፣ በተደረጉ የቡድን ውይይቶች እና በኤግዚቢሽን መልክ ከቀረቡ የተለያዩ ፕሮግራሞች መገንዘብ መቻሉንና ይህም በቀጣይ ለምንወስዳቸው የማህበራዊ ጥበቃ እርጃዎች ከፖሊሲ ክለሳ እስከ ፕሮግራም አተገባበር ባለው ሂደት ለሚኖሩ ስራዎች ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

 

በኮንፈረንሱ የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ፖሊሲ ማዕቀፍ እና የአለም ባንክ ማህበራዊ ጥበቃ ተጋላጭነት ለመቋቋም፣ ለማህበራዊ ትስስር፣ ለልማት ያለውን ሚና እና የልማት አጋሮች የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና በተመለከተ ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ ማግኘት መቻሉን አንስተዋል።

በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ቁጥር እና ተያያዥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ማህበራዊ ትስስርንና የቤተሰብ ሚና ማሳደግ፣ ማህበራዊ ጥበቃን በዘላቂነት ፋይናንስ ማድረግ፣ ውጤታማ የማህበራዊ ዋስትና ሽፋንን ማስፋፋት በሚቻልበት አግባብ እንዲሁም የአደጋ ስጋቶችን በመለየት የአደጋ ስጋት ምላሻችን ለማጠናከር እና የስራ አመራር አስተዋፅኦን ከፍ በማድረግ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለመገንባት እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ውጤታማነት የሚረዱ ተጨማሪ ሃሳቦች መገኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከፓናል ውይይቶቹ ባሻገር ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦች መንግስት ለሚያወጣው የፖሊሲ ማእቀፍ እና ህግጋት፣ ማህበራዊ ጥበቃን ፋይናንስ ለማድረግ፣ የመንግስት እና የግል አጋርነትን ለማጠናከር፣ የመረጃ አያያዝና አስተዳደር ስርዓትን በማጎልበትና ዲጂታላይዝ በማድረግ ለማዘመን የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ኮንፈረንሱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ስርዓት በመገንባት ሂደት የስራ ገበያ ጉዳዮችን በተመለከተ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቁልፍና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች መኖራቸውን እንድናይ አስችሎናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በአግባቡ በመፈተሽ ቀጣይ ለሚደረግ የፖሊሲ ማሻሻያ እንደተጨማሪ ግብዓት መጠቀም እንዲቻል ኮንፈረንሱ መልካም አጋጣሚን እንደፈጠረ ጠቅሰዋል፡፡

በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትሯ ኮንፈረንሱ ዓላማውን ማሳካቱንና እንደሀገር በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለመገንባት ጠቀሜታቸው እጅግ የጎላ ግብዓቶች ማግኘት የተቻለበት እንደነበረ በመግልፀ የሃገር አቀፍ የማህበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንሱ እንዲሳካ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ላሳዩት ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም ስራ ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ የሕፃናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን የምስጋና ምሰክር በመስጠት በኢትዮጵያ መንግስት እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወደፊትም የተለመደ ትብብራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *