Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
“ከፍተኛ የውሣኔ ሰጪነት ቦታ ሴቶች በእውቀት፣ በብቃትና የራሳቸውን ጥረት በማድረግ የሚገኝ መሆኑን ማሳየት አለባችሁ” – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
በሀገራችን ተተኪ ሴት አመራሮችን በማፍራት በውሳኔ ሰጪነት ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከ UNWOMEN ጋር በመተባበር በ6 ዙር ሲሰጥ የቆየው የሴቶች የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት የአቅም ግንባታ ስልጠና የማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሄደ።

በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለሰልጣኞች የቀጣይ አቅጣጫና የስራ መመሪያ የሰጡት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለፁት፤ ከፍተኛ የውሣኔ ሰጪነት ቦታ በሌሎች ቸርነት የሚሰጥ ሳይሆን ሴቶች በእውቀት፣ በብቃትና የራሳቸወን ጥረት በማድረግ የሚገኝ መሆኑን ማሳየት እንዳለባቸው ገልፀዋል ። ክብርት ፕሬዚዳንቷ እንደገለፁት፤ በሀገራችን የሴቶችን የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ ያለውን ችግር በመገንዘብ ይህንን ስልጠና መስጠት እንዳስፈለገ ተናግረዋል ። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አክለውም ሰልጣኞች ጠንካራ ኔትወርክ መፍጠር፣ የወሰድትን ስልጠና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ለሚገኙ ሴቶች ማስተላለፍ፣ በየመጡበት አካባቢ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ሴት ተማሪዎችን ማብቃትና ማገዝ እንዲሁም እርስ በርስ በመተባበርና በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል። ኘሬዝዳንቷ አያይዘውም ይህ አይነቱ ስልጠና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጽህፈት ቤታቸው የተቻለውን ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር በአስር አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡትን ሀገራዊ ግቦችን መነሻ በማድረግ ስራዎችን በቅጅንት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተያዝው በጀት ዓመትም ሊያከናውናቸው በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው የሴት አመራሮችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት ሴቶችን ለማብቃት እያደረገ ያለው ጥረት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡ ሚንስትሯ አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በተለይም ከUNWOMEN ጋር በመተባበር ቀደም ሲል ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከፌዴራል ሴክተር መ/ቤቶች ለተውጣጡ ሴት እጩ አመራሮች የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን ሊያጎለብቱ የሚያስችሉ የተለያዩ የስልጠና ፓኬጆችን መስጠቱንና የሴት አመራሮች ቋቱን ለማስፋት የበኩሉን እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የተዘጋጀውን የሴት አመራር ቋት በየደረጃው ለሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮችና የስራ ኃላፊዎች እንዲያውቁት በማድረግ ለተግባራዊነቱም ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በራሳቸው ተነሳሽነት የመሪነትና የአርዓያነት ሚናቸውን በመወጣት የሃገራችን ነባር ሴት አመራሮችን ጭምር ይህንን ፈለግ መከተል እንዲችሉ ላደረጉትና እያደረጉ ላሉት አስተዋፅኦና ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ሴቶች ካውከስ ሰብሳቢ ክብርት ኪሚያ ጁንዲ በስልጠናው የተሳተፉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴቶች የተሻለ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልፀው በተሰጣቸው ሀላፊነትም ለሴቶች አቅም፣ በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ተግዳሮቶችም የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።በስልጠናው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግስት መዋቅሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የግሉ ሴክተር ሴቶችን ያካተተ የ 6 ዙር ስልጠና እንደነበር ተገልጿል።
