Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የህጻናት መብትና ደህንነት ጥበቃ ስርዓት ለማጠናከር ዩኒሴፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት /UNICEF/ ዳይሬክተር ሽማ ሰንጉብታ እና ልዑካን ቡድናቸውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በቆይታቸውም፥ በህጻናት መብትና ደህንነት ጥበቃ ስርዓትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሰፊው ተወያይተዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜም፥ መንግስት የህጻናት መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን የህጻናት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከልና ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል። በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል። ህጻናት የማህበራዊ አገልግሎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሆኑ ለማስቻል የህጻናት የልደት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

የህጻናት ጥበቃ ስርዓትን የበለጠ ውጤታማ ከማድረግ አኳያም ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት መዘርጋቱን፣ በፓይለት ደረጃ እየተተገበረ መሆኑንና በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስረድተዋል። የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ በሀገራችን በተለይም ደግሞ ግጭት ተከስቶ በነበረባቸው አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት ግልጋሎት የሚውል የአንድ መስኮት መስጫ ማዕከልና የሴቶች ማረፊያ በማቋቋም፣ የተቀናጀ የማህበራዊና ስነልቦና ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ የማህበራዊ ሰራተኞችን አሰልጥኖ በማሰማራት እንዲሁም በገቢ ማስገኛ ዘርፍ እንዲሰማሩና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልጸው በኢትዮጵያ መንግስትና በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነዋል። ድጋፉ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት / ዩኒሴፍ/ ዳይሬክተር ሽማ ሰንጉብታ በበኩላቸው መንግስት የህጻናትን ሁለንተናዊ መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በተለይም ደግሞ የህጻናት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ያሳየውን ቁርጠኝነትና የተገኘውን ውጤት አድንቀዋል።

በቀጣይም የህጻናት ጥበቃ ስርዓት ማጠናከርን ጨምሮ በአጠቃላይ በህጻናት ዙሪያ ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቀረጻቸው ኢኒሼቲቮችና የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ኒውዮርክ በሚገኘው የዩኒሴፍ ዋና ቢሮ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
