Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ሳይነጠሉ ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ እያገኙ እንዲያድጉ ለማስቻል ቤተሰብን የማጠናከር ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል
ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ሳይነጠሉ ፍቅርና ክብካቤ እያገኙ በእውቀትና በመልካም ስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ለማስቻል ቤተሰብን የማጠናከር ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።

ኤስ ኦ ኤስ/SoS/ ኢትዮጵያ የህፃናት መንደር የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዩቤልዮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ ሚኒስቴሩ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በተለይ ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በተለያዩ አማራጭ የድጋፍና እንክብካቤ ፕሮግራሞች ለመደገፍና ተደራሽነቱን ለማስፋት የጀመረውን ሥራ ወደፊትም አጠናክሮ እንዲሚቀጥል ተናግረዋል።

በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ሳይነጠሉ የወላጆቻቸው አሊያም የአሳዳጊዎቻቸውን ፍቅርና እንክብካቤ እያገኙ እንዲያድጉ ማስቻል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። ለዚህም የቤተሰብ ማጠናከሪያ (Family Strengthening) ስራዎችን እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ ኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር ቤተሰብ ተኮር የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ ስርዓቶችን በመዘርጋት የበርካቶችን ህይወት ለመለወጥ እያበረከተ ላለው የላቀ አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል።

የኤስ ኦ ኤስ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር አቶ በድሉ ሸገን ድርጅቱ የተደራሸነት አቅሙን በማሳደግ የብዙዎችን ህይወት ለመለወጥ ሰፊ ራዕይ መሰነቁ ጠቁመው ለስኬታማነቱ አቅም የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ሁሉም እንዲተባበርና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የኤስ ኦ ኤስ ኢትዮጵያ የህፃናት መንደር ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም አበበ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ ባለፉት 50 አመታት በ9 ክልሎችና በ2 የከተማ አስተዳደሮች ከ8.1ሚሊዮን በላይ ህፃናትን፣ ወጣቶችንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።
