Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሆነ።
ኢትዮጵያውያን ሴቶች ያሉበት ደረጃና ቅድሚያ ስለሚሰጧቸው ጉዳዮች ሁኔታ ላይ የተካሄደ ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ይፋ ተደርጓል።

ጥናቱን ላለፉት 2 አመታት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ኔትወርክ፣ኦክስፋም ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ልኡካን ጋር በጋራ በመሆን አከናውነዋል። በዕለቱ የጥናት ሰነድን ይፋ መሆኑን ያሳወቁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እና ሴቶችን ለማብቃት ምቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ በየጊዜው እንደሚያወጣ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ከግማሽ በላይ ስለሚሆኑት ሴቶች እና ስለሴቶች ጉዳይ ያሉት መረጃዎች የተበታተኑ እና የተገደቡ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ እንደገለፁት ይህ ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት የኢትዮጵያ ሴቶች ሁኔታ እና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለመስጠት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል ። ጥናቱ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለሥርዓተ-ፆታ ተሟጋቾች፣ ለመገናኛ ብዙኃን እና ለተመራማሪዎች አጋዥ መሆኑንም ዶ/ር ኤርጎጌ ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጥናቱ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመፍጠርና ለመከለስ ፣ ግንዛቤን ለማሳደግ ፣ ለህዝብ የሚቀርቡ መረጃዎችን ለማሟላት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን በበኩላቸው የዳሰሳ ጥናቱ በዋናነት በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በፆታዊ ጥቃት፣ በሥነ ልቦና፣ በፖለቲካ፣ በዜግነት፣ በሰላም፣ በጸጥታ እና በፍትህ ተደራሽነት ዙሪያ በተለያዩ ዘርፎች ሴቶች ያሉበትን ደረጃ እና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አጠቃላይ መረጃዎችን ለማቅረብ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ አጠቃላይ የዳሰሳ ጥናት በ8 ክልሎች 36,367 ሴቶችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ የተደራጀ ጥናት መሆኑም ተገልጿል።

