በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል 5ሺ የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ተበረከተ።

በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ( ዶ/ር) እንደገለጹት

የወር አበባ ለሴቶች የተፈጥሮ ጸጋና ትውልድን ለማስቀጠል ከፈጣሪ የታደሉት የህይወት ክፍል ቢሆንም በንፅህና መጠበቂያ ምርት ላይ በሚስተዋለው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣የዋጋ ውድነትና ጥራት አለመኖር ምክንያት ሴቶችና ልጃገረዶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ሚኒስትሯ እንደገለፁት ይህ ችግር በይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲዎች ላይ መሆኑን በመገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከመንግስት ጥረት ጎን ለጎን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የግል ባለሃብቶችና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አድንቀዋል። በዛሬው እለትም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ቃል በገባው መሠረት በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ከቱርክ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዳበረከተ ገልፀዋል።

የንፅህና መጠበቂያው ጀረጃውን የጠበቀና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተመረተ መሆኑን ጠቅሰዋል ። በቀጣይም የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ፣ ሁለተኛ ደረጃና በገጠራማው አካባቢ ለሚገኙ ሴቶችም ለማቅረብ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታትና መደገፍ፣ አዳዲስ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲገቡ ማስቻል፣ የአጋር ድርጅቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ በስርጭት ሂደት ያሉ ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝንዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ለሴት ተማሪዎች የተበረከተው ስጦታ የወደፊቷ ባለ ብሩህ አዕምሮ የኢትዮጵያ ሴት ልጆች ለማፍራትና ችግሮችቻቸውን በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የቱርክ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ኃላፊ ኤንቨር ረሱልጉላሪ እንደገለፁት ኤጀንሲው በኢትዮጵያ በጤና በትምህርት በሰብአዊ ድጋፎችን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች እንደሚሳተፍ ገልፀው ይህ የንፅህና መጠበቂያም የትብብሩ አንዱ አካል መሆኑን ገልፀዋል ።በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውለው የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እስከ ሁለት አመት ድረስ እንደሚያገለግል ተገልጿል ።

 

 

Please follow and like us: