የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ ዩኤን ውመን(Un _Women) ረዳት ዋና ፀሐፊ እና ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ላይ ተወያየ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ ዩኤን ውመን ረዳት ዋና ፀሐፊ እና ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት ኒያራድዛይ ጋምቦዝቫንዳ ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ላይ ውጤታማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢትዮጵያ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀረጹና በትግበራ ላይ የሚገኙ የተለያዩ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በመፈረምና የሕጎቿ አካል እንዲሆኑ በማድረግ እየተገበረች እንደምትገኝ ገልፀዋል ። ሚኒስትሯ እንዳሉት ሚኒስቴር መስርያቤቱ የስርአተ ፆታ ምላሽ ሰጪ በጀት፣ (gender responsive budget) እና የስርአተ ፆታ ኦዲት (gender audit) በጾታ እኩልነት እና የሴቶችን አቅም በማጎልበት ረገድ ከ ዩኤን ውመን (un _women) የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው በቀጣይም በተለያዩ የትበብር መስኮች ላይም መስራት እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

ከነዚህም መካከል በሴቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የፓለቲካ ተሳትፎ ላይ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ ለመቀጠል በተለይም ሴቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሴቶችን ለመደገፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን ገልፀዋል። በተጨማሪም የከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ዜጎችን በጊዜያዊነት ከመደገፍ ባለፈ መሠረታዊ የአኗኗር ለውጦችን እንዲያመጡና የመስራት አቅም ያላቸውን ዜጎች ወደ ምርታማነት በማስገባት ለሀገሪቱ ብልፅግናና እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚፈልጉ ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

የዩኤን ውመን( Un Women) ረዳት ዋና ፀሐፊ እና ምክትል ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ኒያራድዛይ ጋምቦዝቫንዳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ሌሎች ሀገራት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ የስርአተ ፆታ ስራዎችን መስራቷን ገልፀው ዩኤን ውመን( Un Women) እስካሁን በትብብር ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ በሌሎች መስኮች ላይም በትብብር ለመስራት ቃል ገብተዋል።

 

Please follow and like us: