ሴቶችና ታዳጊዎችን ከጎጂ ድርጊቶች መጠበቅ የሚያስችል የተለያዩ ስትራቴጂክ ዶክመንቶች ይፋ ተደረጉ

የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴት ልጅ ግርዛት ፈፅሞ ያለመታገስ ቀን “የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ ጥረትን ማፍጠን፣ ጥምረትን ማጠናከር እና ንቅናቄዎችን መፍጠር” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

የሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት ኢትዮጵያ ሰፊ ስራዎችን እየሰራች ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዩኤን ኤፍ ፒ እና ዩኒሴፍ ጋር በመተባበርም ሴቶችና ታዳጊዎችን ከጎጂ ድርጊቶች ለመጠበቅ፣ አቅማቸውን ለማጎልበት፣ የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣትና የተጀመረውን ጥረት ለማስቀጠል የሚረዳ ስምንት ስትራቴጂክ ዶክመንት በዛሬው ዕለት ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በዶክመንቱ ሴቶችና ታዳጊዎችን ከጎጂ ድርጊቶች መጠበቅ፣ የሴቶችን አቅም ማጎልበት፣ የማህበረሰብ ለውጥ ማምጣት፣ የወንዶችን ሚናና ተሳትፎ ማሳደግ የሚሉትና ሌሎች ሀሳቦች መካተታቸውን ገልጸዋል። ዶክመንቱ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በኦሮምኛ፣ በአፋርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ጭምር መዘጋጀታቸውን እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ለመተግበር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። ዶክመንቱን ወደተግባር በመቀየር ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ቀኑን ምክንያት በማድረግ የሴት ልጅ ግርዛት ያለበት ደረጃ፣ የሴት ልጅ ግርዛት ለማስወገድ የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች፣ ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶች/ክፍተቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች በተመለከተ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ ዕለቱን በማስመልከት አጋር አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

Please follow and like us: