Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ከመፋታት ችግሩን መፍታት!

ማህበረሰብም ሆነ ሃገር የቤተሰብ ድምር ውጤት ነው፡፡ የቤተሰብ ምስረታ መሰረቱ የሚጣለው ደግሞ በጥንዶች መካከል በሚፈጸም ቅዱስ ጋብቻ ውስጥ በሚገባ የቃልኪዳን ውል ነው፡፡ ይህ ውል የጥንዶቹን ቋሚ አብሮነት የሚያረጋግጥ ብርቱ ማኅተም ነው፡፡
ይህ የከበረ የቤተሰብ ተቋም በሃገራችን ከምስረታው ጀምሮ ከፍ ያለ ከበሬታ የሚሰጠው ሲሆን እንደየባህሉ በልዩ ልዩ ዝግጅት፣ በሰርግ እና በምርቃት ታጅቦ፣ በህብረተሰቡም እውቅና ተሰጥቶት፤ በአንዲት ሴት እና ወንድ መካከል በሙሉ ፈቃደኝነት በሚመሰረት ጋብቻ የሚጸና ዘላቂ ጥምረት እና ተቋም ነው፡፡ ትዳር የመሰረተ ሰው በህብረተሰቡ የሚኖረው ከበሬታ እና የሚሰጠው ሥፍራ ከፍ ያለ ነው፡፡ ማህበራዊ ተሳትፎው እና ኃላፊነቱም በዛው ልክ ያድጋል፡፡ ባለትዳሮች እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ፣ ትውልድም ያስቀጥላሉ፡፡
ህይወቱን በጋብቻ የሚጀምረው ቤተሰብ በልኩ የተሰፋ የታወቀ ሚና እና ከፍ ያለ ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደህንነቱን የሚፈትኑ ነገሮች ከየአቅጣጫው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በጋብቻ የፀኑትን በማሰብ፣ ልምዳቸውን በመጋራት፣ የህይወት ተሞክሯቸውን በመቅሰም፣ በመነጋገር እና በመደማመጥ ነገሩን ጊዜ ሰጥቶ በማቆየት ትዕግስትን እና ማስተዋልን በማስቀደም በስክነት እና በእርጋታ የትዳር ውስጥ ፈተናዎችን መቋቋም ይቻላል፡፡ ይህ ከጥንዶቹ ከውስጣቸው የሚመነጭ በጓዳቸው የሚዘጋጅ መፍትሔ ነው፡፡
ከፍ ብሎ ነገሩ ከጠነከረ ጉዳዩን በቤተዘመድ በማየት፣ በቅርብ ሰዎች እና በታላላቆች ተሳትፎ በመወያየት አላፊውን ፈታኝ ሁኔታ ሳይሆን መጪውን የቤተሰብ እጣ ፈንታ በማሰብ ለራስም ለልጆችም ደህንነት እና ጤናማ ህይወት መቀጠል ትዳርን ከመፍታት ችግሩን መፍታት እጅግ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡
የጋብቻ ህይወት የከበረ ዋጋ አለው፡፡ ሆኖም ፍቺን እንደ እረፍት እና መፍትሔ መቁጠር አደገኛ ውጤት አለው፡፡ ትዳር እንደ ስራ ውል አይደለም፡፡ በእውቀት እና በክህሎት እንደሚከናወን መደበኛ ስራ በአማራጭ የሚቀየርም አይደለም፡፡ ፍቺ ሲመጣ የሚከተለው የሥነልቦና መታወክ፣ የአባላቱ መለያየት፣ የጥሪት መከፍለ እና ሊከተል የሚችል ፀፀት ሊነበብ የሚችለው በዋናነት ለባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ ፍቺን መቼም ቢሆን መፍትሔ አድርጎ አለማሰብ የጥንዶች ብቃትን ይጠይቃል፡፡
ጋብቻ ከጅምሩ መሰረታዊ ኣላማውን ስቶ ጉዞ ከጀመረ ረጅም ርቀት ላይሔድ ይችላል፡፡ አብዛኛው የፍቺ ምልክትም ይሔው ነው። አንድም ለመረዳዳት የሚመሰረት ጋብቻ በመፍረስ ችግርን ሊሻገር አይችልም፡፡ አልባሌ ሰበቦች የፍቺን መንገድ ሊያቀኑም አይገባም፡፡ ፍቅራቸው ማሰሪያ ገመዳቸው የሆነ ጥንዶች ባልንጀሮቻቸውን ፈጥነው በከንቱ ሊሸሹ አይገባም፡፡ ትዳር የሥነ-ልቦና ጉዳይ ነው። ማሰሪያ አንቀፁ ፍቅር ነው፡፡ ጉዳዩ ትዳር፣ ጉዳዩ ጋብቻ፣ ጉዳዩ ቤተሰብ ነው። ጉዳዩ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ማህበረሰብና ሀገር የመገንባት ጉዳይ ጭምር ነው፡፡
ጋብቻ የቤተሰብ የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡ ይህ አለት በምንም እንዳይናወጥ ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ ለቤተሰብ የሚደረግ ጥበቃ በዋናነት ከራሱ፣ ሲቀጥል ከቅርብ ሰዎች እና ከህብረተሰቡ ብሎም ከመንግስት በሚመነጭ ኃላፊነት የሚከወን ተግባር ነው፡፡
ሃገር የምትሰራው ከቤተሰብ ውስጥ ጀምሮ ነው፡፡ ቤተሰብ እየፈረሰ ሃገር ሊሰራ አይችልምና ከመፋታት ይልቅ ችግሩን አስቀድሞ መፍታትን ጥንዶች መርህ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ መልዕክታችን ነው!
