ኢ- መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ዝውውር እንዲኖር የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ያዘጋጀው የ 2025 ቀጠናዊ የፍልሰተኞች ምላሽ እቅድ በበይነ መረብ አማካኝነት ይፋ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት ፍልሰተኞች ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገሮች፣ ከሌሎች ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ በኩል ዝውውር ሲያደርጉ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ህጋዊ እንዲሆኑ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው። መንግስት መደበኛ የሰዎቸ ፍልሰት አስተዳደር እንዲኖር ከመዳረሻ ሀገራት ጋር ስምምነት ማድረግ፣ ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞችን መደገፍ፣ ወደ አገራቸው የመመለስና የመቀላቀል ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናግረዋል።

ኢ- መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ዝውውር እንዲኖር ለማድረግ የመንግስት ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለጋሾች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከዓለም አቀፍ አጋሮች እና ከልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን ፍልሰት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሥርዓት ያለው እና ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑን ለማረጋገጥ የበኩሏን ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

Please follow and like us: