የኢትዮጵያ ህፃናት ምክር ቤት የ2017 በጀት አመት የስድሥት ወር አፈፃፀም ግምገማ እና የቀጣይ እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ህፃናት ፓርላማ የ2017 በጀት አመት የስድሥት ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ የቀጣይ ስድስት ወራት ረቂቅ እቅድ ላይም በሰፊው በመወያየት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ህጻናት ሃሳባቸውን በነጻነት ከሚገልፁባቸውና የዴሞክራሲን ባህል ከሚለማመዱባቸው መንገዶች መካከል የህጻናት አደረጃጀት የሆኑት የህጻናት ፓርላማዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በየደረጃው የሚገኙ የህፃናት ምክር ቤቶች ለህፃናት የገቡትን ቃል ለመፈፀም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተግረዋል። ለዚህም በየክልሉ ያሉትን ጠንካራና ደካማ አፈፃፀሞችን መከታተልና መደገፍ እንዲሁም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በቀጣይም አደረጃጀቱን የበለጠ የማጠናከር፣ የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት ስራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራና ድጋፍም እንደሚያደርግ ገልፀዋል። ህፃናት ሀገራቸውን የሚወዱና በስነምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ብሎም ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ መብታቸውንም እንዲያውቁ እና ግዴታቸውንም በሚገባ እንዲወጡ ማስገንዘብ ይገባልም ብለዋል።

የህፃናት መብትና ደህንነት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በበኩላቸው፥ የህፃናት ፓርላማዎች ህፃናት በችግሮቻቸው ዙሪያ እርስ በእርስ እንዲወያዩ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ የዴሞክራሲን ባህል ከወዲሁ እንዲለማመዱና በራስ የመተማመን አቅም እንዲያሳድጉ ድርሻው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል። በመሆኑም ህፃናት በራሳቸውም ሆነ በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ ድምፃቸው ጎልቶ እንዲደመጥ፣ በመምከር ሂደትም እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ዕድል መስጠት፣ ማበረታታትና መደገፍ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የዘንድሮው አለም አቀፍ ደህንነቱ የተጠበቀ የህፃናት የበይነ መረብ አጠቃቀም ቀንን አስመልክቶ እንዲሁም በህፃናት ፖርላማ አደረጃጀት ጋይድላይንና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለምክር ቤቱ አመራሮች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተካሂዷል።በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የህፃናት ፖርላማ አመራሮች ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: