የአረጋውያንን መብቶች ጥበቃ፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ

የአረጋውያንን መብቶች፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ሊወጣ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።

የአረጋውያን መብቶች ጥበቃ፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ረቂቅ አዋጅ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠብቀውና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ተሟልተው በክብር ሊኖሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም ተፈጻሚነት መንግስት የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እና የአረጋውያን ድርጊት መርሃ ግብርን ጨምሮ ሌሎች የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማውጣት እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በአረጋውያን ላይ የሚንጸባረቁ የተሳሳቱ አመለካከቶችና የሚከሰቱ መገለሎች እንዲቀሩም የግንዛቤ እና የመብት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሆኖም የአረጋውያን ቁጥር በእጅጉ እያደገና በየጊዜው የሚለዋወጠው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በህይወታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል። በተጨማሪም አሁን ላይ ያለውን የአረጋውያንን ቁጥር የሚያሳይ ትክክለኛ አሃዛዊ መረጃ ያለመኖሩ፣ የቁርጠኝነት ማነስና የቅንጅታዊ ስራዎች መጓደል እንቅፋት መፍጠሩንና በነባሩ አሰራር መብቶቻቸውን በተሟላ መልኩ ለማስከበር አዳጋች እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የአረጋውያንን መብቶች ጥበቃ፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ሊወጣ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታዋ በአፅዕኖት ገልፀዋል።

አረጋውያንን በተመለከተ በየደረጃው ያሉ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ሌሎች የአሰራር ማዕቀፎች በተገቢው መንገድ እንዲተርጎሙ ለማስቻል፣ ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ ለማጠናከር፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና አረጋውያንም የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ የበኩሉን እገዛ ያድርጋል ብለዋል።

በግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ የፌዴራል ተቋማት፣ ከኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር፣ የአረጋውያን ድጋፍና ክብካቤ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ተወካዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: