ሴቶች ከቁጥርና ተሳትፎ በዘለለ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት ይገባል – የተከበሩ ወ/ሮ ዘሃራ ሑመድ

ሴቶች ከቁጥርና ተሳትፎ በዘለለ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ዘሃራ ሑመድ ገለፁ።

ሚኒስቴሩ የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀገራችን ለ49ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል ለማክበር ባዘጋጀው የንቅናቄ እቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል። በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ዘሃራ ሑመድ ባለፉት አመታት መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ መብት ለማስከበር የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሠራቱን ገልፀዋል።በቀጣይም ሴቶች ከቁጥርና ተሳትፎ በዘለለ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈፃሚ አካላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው፥ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶችን መብት ለማስከበር የተካሄደውን ትግልና ውጤት ከመዘከር በዘለለ ቀጣይ ዕድሎችን ለመፍጠርና ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችሉ የንቅናቄ መርሐግብሮች በየአመቱ እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዘንድሮም በዓሉን ምክንያት በማድረግ በኢኮኖሚ ዘርፍ በተለይ የሴቶችን ቁጠባ ለማሳደግና በገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ ለማስቻል እንዲሁም የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀትን የበለጠ ለማጠናከርና ሞዴል ቀበሌዎችን ለመፍጠር ሰፊ ዕቅድ መያዙንን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የጤና ችግር እየሆነ የመጣው የጡትና የማህፀን በር ካንሰር በጊዜ ከታወቀ መከላከል፣ መታከምና መዳን እንደሚቻል ግንዛቤ በማስረፅ ሴቶች የቅድመ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።እንደሀገር ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሴቶችን ሚናና ተጠቃሚ የበለጠ ለማሳደግ የታቀዱትን ተግባራት ለማሳካት ሁሉም በባለቤትነት እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

 

Please follow and like us: