የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአውሮፓ ህብረት የሴቶች ጉዳዮች የሚመለከታቸው ተቋማትን የማጠናከር ፕሮግራምን በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከሆኖት ሶፊ ፍሮመስበርገር ጋር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና ዋና ስራዎች ላይ የጋራ ትብብሮችን ለማጠናከር ያለመ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴቶች፣ በወጣቶች እና ህጻናት እንዲሁም ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች የሚደረጉ የማህበራዊ ጥበቃ ድጋፎችን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

ከዚህም ውስጥ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የሆኑትን “ሴቶች በግብርና” ፕሮግራምን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮችን እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የወጣቶች ስብእና ግንባታ ተቋማት ስራዎችን ዝርዝር ስኬቶች አንስተዋል።

የህብረቱ አምባሳደር ሶፊ ፍሮመስበርገር በበኩላቸው፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰሩ ስራዎችን ስፋት ያደነቁ ሲሆን በተጨማሪም ህብረቱ ድጋፍ ከሚሰጥባቸው የማህበራዊ ጥበቃ ዋና ዋና ፕሮግራሞች (የገጠር እና የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት) በተጨማሪ በተፈቃናዮች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ዙሪያ ህብረቱ ድጋፉን እንደሚቀጥል እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የሴቶችን አቅም የሚያሳድጉ ፕሮግራሞችን እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ወቅት ለረጅም ጊዜ ዝግጅት የተደረገበትን የሴቶች ጉዳዮችን የሚመለከታቸው ተቋማትን ማለትም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች፣ በተለያዩ ተቋማት ስር የሚገኙ የስርአተ ጾታ ዳይሬክቶሬቶች እና ተያያዥ ተቋማትን የማጠናከር ፕሮግራምን ወደ ስራ ለማስገባት ሂደት ላይ መሆኑ ከህብረቱ ጋር ያለ ጠንካራ አጋርነት ውጤት መሆኑ ተገልጿል።

Please follow and like us: