የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚደረግ በረራ ያካሂዳል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ዛሬ ማታ ወደ አቴንስ፣ ዴልሂ፣ ዱባይ፣ ዊንድሆክ፣ ሳኦ ፖሎ እና ባህርዳር ከተሞች እንደሚደረግ አስታውቋል። አየር መንገዱ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ማርች 8ን አስመልክቶ በየዓመቱ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ሲያደርግ ቆይቷል።

ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ ለሚጓዙ ሴት የበረራ ሠራተኞች በአዲስ አበባ በተካሄደው የሽኝት መርሐግብር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ክቡራን ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት ክብርት ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴቶች ብቃታቸውን ያስመሰከሩበት ግዙፍ ተቋም እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ በተለያዩ የስራ ክፍሎች የተሰማሩ ሴቶች ለአየር መንገዱ ያልተቋረጠ እድገት ብሎም ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑን በመጥቀስ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም አየር መንገዱ ሴቶችን በማብቃትና የስርዓተ ጾታ እኩልነት በማስፈን በአቪየሽን ዘርፍ የበለጠ ተሳታፊና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ብቃት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደአገር የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ አድማሱን እያሰፋ ባለበት ወቅት የሴቶች ሚና በላቀ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በወደፊቱ የአየር መንገዱ የልህቀት ጉዞም ሴቶች የመጪው ጊዜ የአቪዬሽን ሙያተኞች ሆነው እንዲቀጥሉ ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በዚህም አየር መንገዱ የሴቶችን ተሳትፎ በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ ይተጋል ነው ያሉት።

Please follow and like us: