Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት እና ለሽያጭ የሚያቀርቡበት እድል መመቻቸት እንዳለበት ተገለጸ።
ዓለም-አቀፍ የሴቶች ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ ዞን አመያ ከተማ በኤግዚብሽን ጉብኝት ተጀምሯል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ የተመሩ ከፍተኛ ሴት አመራሮች በደቡብ ምዕራብ እትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮንታ ዞን የሴቶች ህብረት ሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።የበዓሉ የክብር እንግዳ የሆኑት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ የሴቶችን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ የልማት ህብረቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ አማራጮችን ማላመድ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ያለ ሴቶች ተሳትፎ እንደ ሀገር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ያሉት ወይዘሮ ሁሪያ የመሰርያና መሸጫ ቦታን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ልደረግላቸው ይገባልም ብለዋል። በማህበር ከተደራጁ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ትዕግስት ዶኖቾ፣ ወይዘሮ ጎቶሬ ጎደቶ እና ወይዘሮ ዘይቱ ብሩ ፤ የሌማት ትሩፋት ተግባር በፈጠረው ተነሳሸነት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በኘሮግራሙ በኢፌድሪ ፌዴረሽን ምክር ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የህገ-መንግስት ትርጉም ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ዱባለ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ምስራቅ ማሞና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ ተገኝተዋል፡፡
