Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
እንደሀገር የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማክበርና አካታች በሆነ መልኩ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ ተቋማት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለፀ።
ይህ የተገለፀው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተ.መ.ድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን የተቋማት መገምገሚያ መስፈርትንና ሌሎች አካል ጉዳተኛን የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች ላይ ለፌደራል ተጠሪ ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው።

በመድረኩ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አሳልፈው አመዲን እንደገለፁት እንደሀገር የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማክበርና አካታች በሆነ መልኩ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው ተቋማት ከተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት አንፃር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ለዚህም መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተ.መ.ድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን ያወጣቸው ህጎች ከመቀበል አንስቶ ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ተግባራዊ መሆናቸውንና መንግስት አካል ጉዳተኞችን ማካተትና ማሳተፍ ላይ ትኩረት እድርጎ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህም ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች የተመቹ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ፣ አካታች ፖሊሲዎችን መቅረፅ፣ የተሃድሶ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም እንደ ትምህርት፣ ጤና ያሉ መሠል የማህበራዊ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን አካታችና ተደራሽ ያደረጉ እንዲሆኑና ያለባቸውም ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰት ለመከላከል እና እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል ይህ አይነቱ ስልጠና አስፈላጊነቱን ገልፀዋል ።
በቀጣይም አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች አፈፃፀም በተቋማቱ ላይ የክትትልና ድጋፍ ስራ ይሠራል።
