ብሔራዊ የፍልሰት ኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ እና የፍልሰት የአምስት አመት መሪ እቅድ ዋና ዋና ይዘቶች

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት የአምስት አመት መሪ (ስትራቴጂያዊ) እቅድ እና ብሔራዊ የፍልሰት ኮምኒኬሽን ስትራቴጂ በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።
ብሔራዊ የፍልሰት ኮምኒኬሽን ስትራቴጂው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ሲሆን ግቦቹም ዜጎች መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ያሉት አደጋዎች ላይ እንዲሁም መደበኛ እና ህጋዊ ፍልሰት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በመጨመር መደበኛ እና አስተማማኝ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ማበረታታት እና ታሳቢ ፍልሰተኞችም በአገር ውስጥ ያሉ አማራጭ የኑሮ ዘዴዎቸን እንዲያዩ ማስቻል ናቸው።

በሌላ በኩል የአምስት አመት የጋራ የፍልሰት መሪ ስትራቴጂው ከ2017- 2021 ዓ.ም ድረስ ፍልሰትን አስመልክቶ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በጋራ የሚሰሩበት የስትራቴጂ ሰነድ ሲሆን አላማውም መንግስት የፍልሰተኞች ተጋላጭነትን በመቀነስ እና የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ መደበኛ የሆኑ የፍልሰት መንገዶችን የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር ነው።

የሰነዱ ዋና ዋና መርሆዎችም
• የፍልሰተኞችን ሰብአዊ መብቶቸን ከግምት ውስጥ ማስገባት፣
• ስርአተ- ጾታን ትኩረት ያደረገ ምላሽ መስጠት፣
• የህጻናት ደህንነት እና መብቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት፣
• አለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና አገራዊ ስታንዳርዶችን መሰረት ማድረግ፣
• ቀጣይነት፣ ባለቤትነት እና የማህበረሰብ ተሳትፎን ማረጋገጥ እንዲሁም ግልጽነት እና ተጠያቂነትን መሰረት ማድረግ ናቸው።

ስትራቴጂያው ሰነዱም በዋናነት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል፣ የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃን ማረጋገጥ፣ መረጃ እና ጥናትን መሰረት ያደረገ የፓሊሲ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ማስቻል እና የተለያዩ ፍልሰትን የሚመለከታቸው አካላት አቅም ግንባታን ማከናወን የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው። እነዚህን ተግባራትን ለመፈጸም በጋራ የሚሰሩ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ተለይተው በስትራቴጂ ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እና መለኪያዎቻቸውም በዝርዝር በሰነዱ ተቀምጠዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረጉት ሁለት ሰነዶች የፍልሰት አስተዳደርን የተቀናጀ እና ውጤታማ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ በቅርቡ ይፋ የሚጫኑ ይሆናል።

Please follow and like us: