የአለም ባንክ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የማህበራዊ ጥበቃ ስራ ስኬታማነት አደነቀ

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የማህበራዊ ጥበቃ ስራ ስኬታማ መሆኑን የአለም ባንክ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ማዳም ማርያም ሳሊም ገለፁ።

የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከአለም ባንክ የአፍሪካ ቀንድ (የኢትዮጵያ የኤርትራ የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን) ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም እና ልዑክ ቡድናቸው ጋር በማህበራዊ ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል። የውይይቱ ዓላማ በማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራትና አዳዲስ የትብብር መስኮች ዙሪያ ለመምከርና አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ ነበር።

በውይይቱ፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ መንግስት ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ እንዲያስችል የከተማና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮግራሞችን ከባንኩ ጋር በጋራ በመቅረጽ ለስኬታማነቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በአለም ባንክ ድጋፍ በመተግበር ላይ ያለው ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ፕሮግራም አፈጻጸምም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲና ስትራቴጂ ክለሳ፣ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ተጠቃሚዎች ምዝገባ ስርዓት ዝርጋታ እንዲሁም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ፕሮግራምን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ያካተቱ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች በመቀረጽ ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል። ለፕሮግራሙ ስኬታማነት አለም ባንክ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን በመጥቀስ ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል። የአለም ባንክ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ማዳም ማርያም ሳሊም በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የማህበራዊ ጥበቃ ስራ ስኬታማና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ባደረጉት ጉብኝት መመልከታቸውን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ የሚያካሄደውን የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት የበለጠ ለማጠናከርና ቀጣይ ፕሮግራም ቀረጻዎች ላይም የአለም ባንክ በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

Please follow and like us: