Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
እናት ባንክ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የፕሮግራም ፓኬጆች በመቅረጽ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው – ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ከእናት ባንክ የቦርድ አመራሮችና የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት መካሄዱን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ክብርት ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ ባንኩ የተቋቋመበት ዋና አላማም ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ባሻገር የሴቶችን የፋይናንስ ማነቆ በመፍታት በተሠማሩበት የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ብቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል። ከዚህ አንጻር ባንኩ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የፕሮግራም ፓኬጆች በመቅረጽ ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት እየተገበረች ላለችው የፋይናንስ አካታችነት (Financial Inclusion) ስርዓት የእናት ባንክ ስራ ተምሳሌት እንደሆነና ልምድና ተሞክሮው ሊቀመር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም ከእናት ባንክ ጋር ያለውን የትብብርና የቅንጅት ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናግረዋል።
Please follow and like us:
