በሀገራችን በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ በተጠኑ የህግ ክፍተቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዩች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ አባላት፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀገራችን በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ በተጠኑ የህግ ክፍተቶች ዙሪያ ውይይት ተደረገ።

በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲሆን፣ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ህጎች ቢኖሩም አሁንም በህጎቹ ላይ ክፍተቶችና ግልጽነት የጎደላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል። በዚህም ምክንያት ተጎጂዎች ፍትህ እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው እነዚህን ክፍተቶች መለየትና ማረም አስፈላጊ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል።

 

በዋናነትም በሀገራችን በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ ያሉ የህግ ክፍተት ግልፅነት ከማጣት ፣ አሻሚ ትርጉም ከመኖር እና ቅጣቶች ከማነስ አንጻር በመለየት የህግ ማሻሻል እንዲደረግባቸው ምክረ-ሃሳብ ማቅረብ ዋና አላማው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችና ችግሮች ለመፍታት፥ ዘላቂ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት፥ ማንኛውም ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ምንም ተቀባይነት እንደሌለው ለማረጋገጥና ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለመጠበቅ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተለይም ለጉዳት የተጋለጡ ግለሰቦችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ጠንካራ የህግ ማዕቀፍና አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀትና ፖሊሲ ኢትዮጵያ ከገባቻቸው እንደ የቤጅንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ-ግብር፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልዎችን ለማስወገድ የወጣው ስምምነት ፣ የሕፃናት መብቶች ስምምነት የማፑቶ ፕሮቶኮል፣ የዘላቂ ልማት ግቦች እና ሌሎች አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችና ሀገራዊ እቅዶች ጋር ለማጣጣም፣ እንዲሁም በወቅታዊ የሁኔታ ዳሰሳና ክፍተቶች ላይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ፆታን መሠረት ያደረገጥቃት ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት መሰረት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ውይይቱ በዋናነትም በሀገራችን በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ ያሉ ህጎች ክፍተት ግልፅነት ከማጣት ፣ አሻሚ ትርጉም ከመኖር እና ቅጣቶች ከማነስ አንጻር በመለየት የህግ ማሻሻል እንዲደረግባቸው ምክረሃሳብ ማቅረብ ዋና አላማው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

Please follow and like us: