Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሐግብር ዝግጅት ሂደት ላይ ስትሪንግ ኮሚቴው ውይይት አካሄደ
የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሐግብር ዝግጅት ሂደትና በቀጣይ ትኩረት በሚሰጣቸው ጉዳይ ዙሪያ ስትሪንግ ኮሚቴው ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የቴክኒክ ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት የተመለከተ ሪፖርት ለዓብይ ኮሚቴው አቅርቧል።
በሪፖርቱ ከአማራ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሱማሌ ክልል በስተቀር ለድርጊት መርሐ ግብሩ የቅድመ ጥናትና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ መሠራቱን፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሠጠቱን፣ በየደረጃው ውይይትና ምክክር መደረጉን እና ረቀቅ ሰነድ መዘጋጀቱና ግብዓት እየተሠጠበት መሆኑ ተገልጿል።

በውይይቱ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን በግጭት ወቅት ሴቶችና ህፃናት የበለጠ ተጎጂ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሴቶች ብዙ አቅም አላቸው በሚገባ መጠቀምና ተሳትፏቸውንም ማሳደግ ይገባል ብለዋል። በተለይ በግጭት መከላከል፣ በሰላም ጥበቃ፣ በግጭት አፈታትና በሰላም ግንባታ ረገድ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ማጉላት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ለዚህም የድርጊት መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንና ሴቶችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።

ለድርጊት መርሐ ግብሩ ዝግጅትና ስኬታማ ትግበራ ባለድርሻና አጋር አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
የሴቶች አጀንዳ ከንግግር ባለፈ ገቢራዊ ስራን ይጠይቃል ያሉት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዋና ስራ አስፈፃሚ አጥናፉ ወርቁ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ ሴቶችን አካታችና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚቴው በተቀሩት ክልሎች የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱን ማስቀጠል፣ መደበኛ የግንኙነት ጊዜን መወሰን፣ ለትግበራው የሚያስፈልግ ሀብት ማሰባሰብ እና የቅንጅትና የአድቮኬሲ ስራዎች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
