እንደሀገር በኅብረት ሥራ ቁጠባና ብድር ዘርፍ የተደራጁ ሴቶች ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ ችለዋል – የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን

ሴቶች በኢኮኖሚ እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ከራሳቸውና ከቤተሰብ ባለፈ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ረገድ የበኩላቸውን አሻራ በማሳረፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ይታመናል።

በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሏቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በጋራ ለማቃለል የጋራ ዓላማ ሰንቀው ፍላጎታቸውን ለማሟላት ደግሞ በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው መንቀሳቀስ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው።የኅብረት ሥራ ማህበራት የአባላትን የቁጠባና የስራ ባህል ለማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንዲሁም ያላቸውን እውቀት፣ ጉልበትና ሀብት በማቀናጀት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ተቋም መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ ገልፀዋል።

ይህን የተገለፀው እንደሀገር በተለይ በቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር የተደራጁ ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚገኝበትን ደረጃ አስመልክተው ለክልልና ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ማህበራዊ ሴክተር የስራ ሃላፊዎች ገለፃ በተደረገበት ወቅት ነው። እንደስራ አስፈፃሚው፥ ኅብረት ሥራ ማህበራት ከአባላት ተጠቃሚነት በተጨማሪ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። በተለይ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሀገር እየተደረገ ባለው ጥረት በአሁኑ ወቅት በኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፍ የሴቶች የአባልነት ተሳትፎ 37 በመቶ፤ የአመራርነት ተሳትፏቸው ደግሞ 18 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በኅብረት ሥራ ቁጠባና ብድር ዘርፍ በአጠቃላይ ከተቆጠበው ከ57.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 46 በመቶው ያህሉ የተቆጠበው በሴቶች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ በ2016 በጀት ዓመት ብድር ካገኙ አባላት መካከል ሴት አባላት 44 በመቶውን እንደሚሸፍኑም አመልክተዋል። ከዚህም ባሻገር ሴቶች በወሰዱት ብድር በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማምጣት መቻላቸው ብቻም ሳይሆን በብድር አመላለስ እና በኦዲት ሪፖርት ረገድም በእጅጉ የተሻለ አፈፃፀም እንዳላቸው ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በኅብረት ሥራ ዘርፍ ጠንካራና ለሌሎች ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ሴቶች ቁጥር እየተበራከቱ ቢሆንም በቀጣይ አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል። እንዲሁም በቆጠቡት ልክ ብድር ወስደው በመስራት ረገድ ያለባቸውን ማነቆ የሚፈታ አሰራር በመዘርጋት፣ በማዘመንና የበለጠ ምቹ ማድረግና በሚጠበቀው ልክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በመላኩ ባዩ

Please follow and like us: