የሴቶች አደባባይ ላይ የተገነባው ሐውልትና ትርጉም

በአዲስ አበባ የነበረው የሴቶች አደባባይ ስያሜውን ካገኘ ቆየት ቢልም የሴቶችን ሚና ሊያሳይ የሚችል ምንም የተለየ መገለጫ አልነበረውም፤ አካባቢውም ለዓይን ማራኪ ያልሆነ ነበር።

በካዛንቺስ መልሶ ማልማት ሥራ ግን ይህ አደባባይ ስሙን በተግባር እንዲገልጥ ተደርጎ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በሚገልጽ መልኩ ተገንብቷል።

 

 

ለመሆኑ የሐውልቱ ትርጉም ምንድን ነው?

የሐውልቱ ሐሳብ ሩቅ የምትመለከት እና በእጇ ሚዛን የያዘች ሴት ምሥል ሲሆን የቆመችበት ችቦ ደግሞ ድልን ያሳያል።በአበባው ላይ ከዝቅተኛ ሥራ እስከ ትልቅ ኃላፊነት በተለይም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ዘርፎች እስከ መሪነት ድረስ ሴቶች ያላቸውን ሚና እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ ነው የተሠራው። በዙሪያው የሚታየው የሴቶች ምሥል፣ ሴቶች የኢትዮጵያን ብዝኃነት፣ ማኅበራዊ ትሥሥሮችን እና ባህሎችን በማንፀባረቅ በኩል ያላቸውን አይተኬ ሚና ያሳያል።

በአደባባዩ ግራ ቀኝ የሚታዩት ምሥሎች የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ እያወለበለቡ ከፍ ያደረጉልንን የሴት አትሌቶቻችን ጉልህ ሚና እና የኢትዮጵያን ነፃነት በማስጠበቅ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሴት አርበኞች ተጋድሎን የሚዘክሩ ናቸው። በአደባባዩ ግራ እና ቀኝ የእንዝርት እና እንጀራ ሲጋገር የሚያሳዩ ምሥሎች የተለየ ትምህርት እና ሥልጠና ሳኖራቸው እናቶቻችን ጥጥ አባዝተው፣ ፈትለው እና ወደ ልብስነት ቀይረው የሚያለብሱ እንዲሁም እንጀራ ጋግረው የሚመግቡ በተፈጥሮ የተቸራቸውን ጥበብ እና የላቀ መረዳትን የሚያመላክት መሆኑን ኢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

“ሴትን ማክበርና ማብቃት ሀገርን የማበልፀግ መሠረት ነው”!!

Please follow and like us: