Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ውጤታማ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ውጤታማ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ።

በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉ አስፈፃሚ አካላትን አቅም ለማጎልበት ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። በመድረኩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ቴክኖሎጂ ለአገር ልማት የሚያመጣውን ትሩፋት በመገንዘብ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል። የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025″ ስትራቴጂ በዋናነት የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገቶች ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል። መንግሥት በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአገልግሎት፣ በፋይናንስና በሌሎችም ሴክተሮች ምቹ የዲጂታል ከባቢን በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደሀገር እየለሙ ያሉ ሲስተሞች የጠራ መረጃ ከማደራጀት በተጨማሪ ስራን ያቀላጥፋል፤ ምርታማነትን ያሳድጋል፣ የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን መነሻ በማድረግ አሰራሩን ወጥ፣ የተናበበና ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚጓዝ እንዲሆን ለማስቻል ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል። የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ውጤታማ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል። ለዚህም ሁሉም በየዘርፉ እንዲረባረብ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
