Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሚዲያ አካላት ለቤተሰብ መልካም እሴት ግንባታ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
የሚዲያ አካላት ለቤተሰብ መልካም እሴት ግንባታ ትኩረት እንዲሰጡ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ጥሪ አቀረቡ።

ጥሪው የቀረበው በቤተሰበ ጉዳይ ዙሪያ የሚከበረውን የቤተሠብ ቀን ምክንያት በማድረግ ከሚዲያ እና ከክልል የዘርፉ ባለሞያዎች ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በተዘጋጀበት መድረክ ተገኝተው መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው። ሚኒስትር ዴኤታዋ የቤተሰብ ጉዳዮች ትኩረት አግኝቶ እንዲሰራበት ከህገ-መንግስቱ ዕውቅናና ከለላ በተጨማሪ የአስፈጻሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሥራውን በሃላፊነት ወስዶ እየተገበረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ ለስኬታማነቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ቢሆንም የመገናኛ ብዙሃን ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀዋል:: ሽፋን በመስጠትና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ መልካም ጅማሮ ቢኖሩም በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለማህበረሰብም ሆነ ለሀገር መሠረት የሆነውን የቤተሰብ መልካም እሴቶች ለመገንባትና ትውልድን ለመታደግ የሚዲያ አካላት የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም በመልካም ስነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ ሲኖር በኢኮኖሚ የተገነባ አገር ይኖራልና የሚዲያ አካላት የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጎለብት መስራት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቤተሰብና አረጋውያን ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ወደፊትም ከሚዲያ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያጠናክርና አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በመድረኩ ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ በክልሎች እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ የልምድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን በሚዲያ ሚና ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በመጨረሻም የቤተሰብ መልካም ግንኙነት ከተጠናከረ ለአገራዊ ምርትና ምርታማነት መጎልበት አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የቤተሰብ አባል በልኩ(በአቅሙ) በስራ ሲሳተፍ የቤተሰቡ ኢኮኖሚ ማደግ ስለሚችል እስከታችኛው የህብረተሠብ ክፍል ድረስ የማስገንዘብ ስራውን አጠናክሮ ለማሰቀጠል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
