ኢትዮጵያ 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዷ ተገለፀ።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴቶች ቢዝነስ ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ማውረን ሱምቤንና

የጋራ ገበያውን የስርዓተ ፆታና ማህበራዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ቢትሪስ ሀሞዶንዴ ተቀብለው አነጋግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሴቶች ከፖለቲካ ተሳትፎ ባሻገር ትልቅ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች መሆናቸውን እንደሚያምን ገልፀው ለዚህም የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። በተለይም ሴቶች በግብርና፣ ንግድና ፣የልማት ማህበራት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን በተለያዩ መስኮች በመደገፍ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ቀጠናዊ የንግድ ትስስርን ለማጠነከር የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴቶች ቢዝነስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነቱን አሳውቀዋል ።

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴቶች ቢዝነስ ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ማውረን ሱምቤ፥ኢትዮጵያ 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዷን ጠቅሰው ለተደረገላቸው አቀባበልም አመሰግነዋል። በተጨማሪም ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ ዕድሉን ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረፍ ከአባል ሀገራት ጋር በትስስር በመስራት ላይ እንደሚገኝና ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋርም በጋራ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል።

 

Please follow and like us: