Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ቤተሰብ በተነቃቃ የስራ ባህል ጥሪት በማፍራትና ኢኮኖሚውን በመገንባት ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ብሎም ለሀገር ግንባታ የጎላ አስተዋፆ ያበረክታል- ሚኒስቴር ዴኤታ ሁሪያ አሊ
የቤተሰብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለፌደራል ተቋማት ግንዛቤ ማስጨበጫና ምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ቤተሰብ፤ ትውልድን የመተካትና የማስቀጠል፣ የልጆችና የታዳጊዎችን ስብዕና በመገንባት መልካም ዜጋን የማፍራት ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።ቤተሰብ የህብረተሰብ የተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ እንደመሆኑ የህብረተሰቡንም ትስስር ይበልጥ በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተሰብ በተነቃቃ የስራ ባህል ጥሪት በማፍራትና ኢኮኖሚውን በመገንባት ከራስ ባለፈ ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ብሎም ለሀገር ግንባታ የጎላ አስተዋፆ ያበረክታል ብለዋል።

የዘንድሮው የቤተሰብ ቀን በዋናነትም ትኩረት የተሰጠው የቤተሰብን አኮኖሚ አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል። በገጠርም ሆነ በከተሞች የቤተሰብ የሥራ ባህል እንዲሻሻል፣ እንዲለወጥ እና እንዲያድግ፤ የቤተሰብ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንዲጠናከር፣ የቤተሰብ የስራ እና የኑሮ ሁኔታ እንዲመጣጠን፣ በኢኮኖሚ ምክንያት በቤተሰብ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚያስችሉ እውቀት፣ ልምድ እና አሰራሮችን በመፈተሽ የተሻለ የቤተሰብ ገቢ እንዲፈጠር በየደረጃው የግንዛቤና ንቅናቄ ስራ ይሰራል ብለዋል። የፌደራል ተቋማትን ከየራሳቸው አንፃር በማየት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቤተሰብን በተመለከተ የተሠጠውን ሃላፊነት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ የትግበራ ስልቶች፣ የትኩረት አቅጣጫዎች እና ዝርዝር ተግባራትን በመለየት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝም በዕለቱ ተጠቅሷል።
