የቤተሰብን የስራ ባህልና ገቢን በማሳደግ በሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ በላድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

የቤተሰብን የስራ ባህልና ገቢን በማሳደግ ራስን ከመደገፍ በዘለለ በሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ በላድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስቴሩ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ”የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ለሀገር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐግብሮች እየተከበረ ነው። በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ መንግሥት የቤተሰብን ደህንነትና ምርታማነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና መዋቅሮችን በመዘርጋት በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ቤተሰብን የተመለከተ የሥራ ክፍል በማደራጀትና የአሰራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ የአስፈፃሚ አካላትን አቅም በማጎልበት እና የአድቮኬሲ ስራዎች እየሰራና ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የቤተሰብ ቀን ሲከበርም የቤተሰብን ኢኮኖሚያዊ ሚና ለማሳደግ፣ ለችግር የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሰብና ለመደገፍ አፅዕኖት መሠጠቱን ገልጸዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑና ድጋፍ የሚሹ ቤተሰቦች እንዲቋቋሙና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ በርብርብ መስራትና የተጀመረውም ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በተጨማሪም አስፈፃሚ አካላት የቤተሰብን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት፣ የመስሪያ ቦታና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታትና የአምራችነት ሚናቸውን ለማሳደግ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩና በቁርጠኝነት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋዊያንና ቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው ቤተሰብ የማህበረሰብና የሀገር መሠረት በመሆኑ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል።

 

ቤተሰብ አምራች ሲሆን አገር ምርታማ ትሆናለች ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይም ሀገር እንዲፀና የቤተሰብ ሁለንተናዊ ብልጽግና፣ ደኅንነት እና ዘላቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።

Please follow and like us: