Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ፍልሰትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ተቋማት እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ
ፍልሰትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በግንዛቤ ፈጠራ የስራ ቡድን በተከናወኑ ተግባራት፣ በተመዘገቡ ውጤቶችና በታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ ግመገማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተና በዜጎች ላይም እየደረሰ ያለው ጉዳት እየከፋ መምጣቱን ተናግረዋል። የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአስከፊነቱ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታት፣ ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እንዲሁም አሰራሩ በዘመናዊ መንገድ በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ድርጊቱን የመከላከል ስራ ዘርፍ ዘለልና የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረትን ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ የግንዛቤ ፈጠራ የስራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንና ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የተለያዩ ተግባራት ሲያከናወን መቆየቱን ገልፀዋል። ሆኖም ከችግሩ ስፋትና ከሚጠበቀው ውጤት አኳያ በቂ አለመሆኑንና ተናቦ በመስራት ረገድም ውሱንነት መኖራቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የጥምረቱ አባል ተቋማት በቀጣይ ፍልሰትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና የተጎጂዎችን ሰብአዊ ክብር ለማስጠበቅ በሚደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጡና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል። የሚዲያ ተቋማትም ካላቸው ሰፊ ተደራሽነት አንጻር የመረጃ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የሚያግዙ ቋሚ ይዘቶችን በእቅዳቸው አካተው ሊሰሩና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውንም ሊወጡ እንደሚገባበ አስገንዝበዋል፡፡
