የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢንክሉሲቭ ኢትዮጵያዊ እና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት የፌደሬሽ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ የሆኑት አቶ ሲሳይ ጥላሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞች በሃገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተካታች፣ የእኩል ዕድል፣ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን በቴክኒክ፣ በአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና በፋይናንስ ለመደገፍና ለማጠናከር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞችን መብቶች የሚያስከብሩ ህጎችና ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ የአሰራር ሰርዓትና አደረጃጀት በመዘርጋት ለተፈፃሚነቱ የክትትል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው ረቂቅ ፖሊሲው የጥረቱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

እንደሀገር አካል ጉዳተኞችን የተመለከተቱ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ጉዳዩን በባለቤትነት እና በኃላፊነት መያዝ፣ አዎንታዊ አመለካከትና ግንዛቤ ማዳበር እንዲሁም ለተጨባጭ ለውጥ በቁርጠኝነት መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የሚኒስቴሩ የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውርና ተመላሽ ዜጎች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ በበኩላቸው በብሔራዊ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆን የህግ ማዕቀፍ ለማሰናዳት በቅድሚያ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ፖሊሲው ከመፅደቁ በፊት ባለድርሻ አካላት ሊወያዩበትና የማዳበሪያ ሃሳብ ሊሰጡበት ይገባል ያሉት ስራ አስፈፃሚው የረቂቅ ፖሊሲውን አጠቃላይ ይዘት፣ አስፈላጊነት፣ የትኩረት መስኮች፣ የማስፈፀሚያ ስልቶች እና ተያያዥ ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበው በተሳታፊዎች ግብዓትና አስተያየት ተሰጥቶበታል።

Please follow and like us: