የፊስቱላ ተጠቂዎችን ህይወት ለመታደግ የታሰበ የገቢ ማሰባሰቢያ ተካሄደ።

በምሽቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለፁት በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላን ሙሉ በሙሉ

መከላከል እንደሚቻል፤ ጥራቱን የጠበቀ የእናቶች ጤና አገልግሎትን በማቅረብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮች ፊስቱላን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ለማስወገድ እንደቻሉ ጠቅሰው ኢትዮጵያ ውስጥም ፊስቱላን ለማጥፋት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።በምሽቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሂክማ ኸይረዲን በበኩላቸውየፊስቱላ ችግር የሕክምና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ፍትህ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦና እና በኢኮኖሚ እንክብካቤ የተጎዱ ሴቶችን ለመርዳት ማህበራዊ ኃላፊነት፣ ለመወጣት በፊስቱላ የተጎዱ ሴቶች ህይወትን ወደነበረበት ለመመለስ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግ ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ካለን ትልቅ ሀብታችን አንዱ ትብብርና ቅንጅትን ማሳደግ አንድ መፍትሔ መሆኑን የዛሬው ዕለት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን ችግር ለማስቆም መንግስታዊ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና የልማት አጋሮች በእንድ ላይ በመቀናጀት ዘላቂ እና ተፅእኖ ያላቸውን መፍትሄዎች በመፍጠር መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ህዝብን ያማከለ መፍትሄዎችን ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ሲሆን የሀገር ውስጥ ተቋማት በማስተባበር፣ ማህበራዊ ንቅናቄዎች እንዲካሄዱና መፍትሔዎቹ በአገር ውስጥ ዕውቀት፣ ባህላዊ እሴቶች እና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የበለጸገ ማኅበራዊ ትስስር በመጠቀም በዚህ አውድ ላይ በመመስረት ተጎጂዎች ተገቢው አገልግሎትና ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ፊስቱላ በወሊድ ወቅት የሚከሰት አንዲት ሴት ህይወትን ወደዚህ አለም በማምጣት ሂደት ውስጥ ሊገጥማት የሚችል አስከፊ ጉዳት ነው፤ ችግሩ የሚከሰተው በተገቢው ሰአት አስቸኳይ የወሊድ አገልግሎት ካለማግኘት የተነሳ በሚፈጠር የተራዘመ ምጥ አማካኝነት ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ብዙ ሴቶች ሽንትና ሰገራ የመቆጣጠር ችግር፣ እንዲሁም ረጅም ጊዜ ለሚቆይ አካላዊ ስቃይ ከመዳረጋቸዉም በላይ ለእድሜ ልክ ስነ-ልቦናዊ ችግርና መገለል ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡

በዝግጅቱ ላይ አምባሳደሮች፣ አጋር አካላት፣ የግሉ ዘርፍ ተቋማት እንዲሁም የሀገር ባለሀብቶች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በዕለቱ ከጉዳት አገግመው የጥንካሬና ፅናት ተምሣሌት የሆኑ ታሪኮች ቀርበዋል።

Please follow and like us: