በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሰው ሀብት ኦፕሬሽን ፕሮጀክት (Human capital operation project) ሊተገበር መሆኑ ተገለፀ

በፕሮጀክቱ አተገባበርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ለአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ሲሳይ ጥላሁን ፕሮጀክቱ በተለይ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት በደረሰባቸው አካል ጉዳተኞች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል። ፕሮጀክቱን ወደ ስራ ለማስገባት ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት የመለየትና መረጃ የመሰብሰብ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል። ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በአገሪቱ በተመረጡ 65 ወረዳዎች ላይ እንደሚተገበር አስታውቀዋል። ለተግባራዊነቱም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና ትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ሲኒየር ክትትል ግምገማ፣ ተጠያቂነት ጥናት እና ትምህርት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ንጉሴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ድህነትን ለማስወገድና ምርታማነትን ለማጎልበት እንዲሁም ለእውቀትና ክህሎት መሻሻል የሚያስፈልገውን መዋለ ንዋይ በስራ ላይ ማዋል ተቀዳሚ አላማና ተግባሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ምክንያት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንደትምህርት፣ ጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና ሌሌች ማህበራዊ አገልገሎቶችም አካታችና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽና ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል። ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የዳሰሳ ጥናት ለማከናወን የተዘጋጀው መጠይቅ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ተጨማሪ ግብዓትና አስተያየቶች ተሰጥቶበታል።

 

Please follow and like us: