Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲው ላይ ገንቢ ግብዓቶች መሠጠቱ የፓሊሲውን ውጤታማነት እንደሚያሳድግ ተገለፀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና የማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ ከፌደራል የተዉጣጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ፍትህ ቢሮ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ተጨማሪ ግብአት የማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል።

በዕለቱ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ም/ል ሰብሳቢ ክቡር ታደለ ቡርቃ (ዶ/ር) እንደገለጹት እንደሃገር የፌዴራል አስፈጻሚ ተቋማት የአሰራር ስርዓት ሲዘረጋና የተቋማት አደረጃጀት ስንፈጥር ወቅታዊው የአካል ጉዳተኞችን አጠቃላይ መረጃ ወደጎን ሊተው እንደማይገባና ከአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ውጭ በሆነ መንገድ ዘላቂ የሆነ የሃገር ልማትና እድገት ማምጣት የሚሠጡት ግብዓቶች ጠቃሚና የፖሊሲውን ውጤታማነት እንደሚያሣድግ ጠቅሠዋል ፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲው ላይ የሚሠጡ ግብዓቶች የሃገራችንን አቅም ያገናዘቡ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸው ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የአካል ጉዳተኞችን ወቅታዊ መረጃ ፣ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ፣ ተቋማዊነት ፣ ዘላቂ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጉዳዮች አጽንኦት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤት ክብርት ሁሪያ አሊ በበኩላቸው ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲን ተከትሎ በቀጣይ ይጸድቃል ተብሎ ለሚጠበቀው የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ህግ መነሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል ። አክለውም ባለድርሻ አካላት የሚሠጡት አስተያየትና ግብዓት ፓሊሲው ለውጥ እንዲያመጣ የበኩሉን እንደሚያበረክትም ገልፀዋል።

የዚህ ፖሊሲ ዋና አላማም የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል። በመድረኩ በቀረበው የመወያያ ጽሑፍ ላይ የፖሊሲው መነሻ፣ ፖሊሲውን የማውጣት አስፈላጊነት ፣ መርሆዎች፣ ዋና ዓላማ፣ ዝርዝር ዓላማዎች፣ የማስፈጻሚያ ስልቶችና የአስፈጻሚ አካላት ተግባርና ሃላፊነቶች በዝርዝር ቀርበው በርካታ ሀሣቦች በግብዓትነት ተሠጥቷል።
